በትግራይ ክልል በሚካሂደው የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሕብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቀጣይ በትግራይ ክልል በሚያካሂደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በነቃ ተሳትፎ ሀሳቡን እንዲገልፅ ጥሪ ቀረበ፡፡
የኮሚሽኑ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ ግርማሞገስ ጥበቡ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳትፎ ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም አካላት ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲገልፁ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ኮሚሽኑ እስካሁን በ11 ክልሎች እና ሁለት ከተማ መስተዳደሮች አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራዎችን ማከናወኑን አስታውሰው፤ በቀጣይ ደግሞ በትግራይ ክልል እና በኢትዮጵያዊያን ዲያስፓራዎች እንደሚያካሂድ ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ ከሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ነጋዴዎች ጋር አስቀድሞ የውይይት መድረክ ይካሄዳል ብለዋል።
የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው ከሌሎች ክልሎች ተሞክሮ በመውሰድ በትግራይ ክልልም ከእያንዳንዱ ከተሞች እና ክላስተሮች ውጤታማ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደቱን ይጠቅማሉ ብሎ ያመነባቸው ተሞክሮዎች እና ተቋማዊ እውቀቶች ከተለያዩ አካላት እያካበተ መቆየቱንም ተናግረዋል።
በሚዛን መኮንን