Fana: At a Speed of Life!

ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስራ ስኬታማነት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስራ ስኬታማነት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የከተማዋን ሠላምና ፀጥታ ስጋት ላይ የሚጥሉ ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ጥብቅ ቁጥጥርና ፍተሻ እንደሚያደርግ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በሰጠው መግለጫ መላው የፀጥታ አካላትና ነዋሪው በመተባበር ባከናወኗቸው ተግባራት የከተማችን ሠላምና ፀጥታ በመረጋገጡ ህብረተሰቡ የዕለት ከዕለት ተግባሩን ያለ ስጋት እንዲያከናውን ማድረግ ተችሏል ብሏል፡፡
ነዋሪው የከተማው የፀጥታ ጉዳይ ይመለከተኛል በሚል መንፈስ አካባቢውን በየተራ በመጠበቅና ህገወጦችን እጅ ከፍንጅ ይዞ ህግ ፊት የማቅረብ ልምዱ እያደገ መምጣቱን መግለጫው አመልክቷል፡፡
የፀጥታ አካላት ባከናወኗቸው ልዩ ልዩ ተግባራት በመዲናዋ የወንጀል ቁጥርንም መቀነስ መቻሉንም አንስቷል፡፡
ፖሊስ በደረሱት ጥቆማዎችና በጥናት በለያቸው ሠላምና ፀጥታን ስጋት ላይ የሚጥሉ ከባድ ወንጀሎችንና የወንጀል ስጋቶችን ሙሉ ለሙሉ በመቆጣጠር አጥፊዎችንና ተባባሪዎቻቸውን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል የተጠናከረ ቁጥጥርና ፍተሻ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን የመሳሰሉ የወንጀል ድርጊቶች ይፈፀምባቸዋል ተብለው በሚጠረጠሩና በተለዩ በሁሉም አካባቢዎች የህግ አግባብን ተከትሎ ፍተሻና ብርበራ እንደሚያደረግ ገልጿል፡፡
ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግና ወንጀል እንዳይፈፀም ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የተለመደውን ጥቆማ የመስጠት ተግባሩን እንዲያጠናክርም ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች በ991 እና 8882 ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ፖሊሳዊ መረጃና ጥቆማ እንዲሰጡም ፖሊስ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.