ህዝቡ በሀሰተኛ መረጃ ሁከት ለመፍጠር በሚሞክሩ አካላት መሸበር የለበትም – መሀመድ እድሪስ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች ሽብርና ሁከት ለመፍጠር በሚያሰራጩት ሀሰተኛ መረጃና ማደናገሪያ ህዝቡ መሸበር እንደሌለበት የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ አሳሰቡ፡፡
ሚኒስትሩ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፥ በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በትግራይ ክልል ያለው የሰላም ሁኔታ መሻሻሉን ገልጸው፥ በክልሉ የመማር ማስተማርን ጨምሮ መደበኛ እንቅስቃሴዎች በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠላቸውን አንስተዋል፡፡
በአማራ ክልል ከሁለት አመት በፊት ከነበረው ሁኔታ የተሻለ የሰላም አየር መኖሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ በክልሉ የሚገኙ 22 ዞኖችና የዞን ከተሞች ሙሉ ለሙሉ ሰላም መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ክልሉ ሰፊ ከመሆኑ ጋር በተገናኘ ችግርና ሁከት ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላት ቢኖሩም ተጽእኖ እንደሌላቸው ነው ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ የተናገሩት፡፡
ለተገኘው ሰላም የክልሉ የጸጥታ መዋቅርና የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ በፊት ከነበረው የሰላም መደፍረስ በመላቀቅ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩንም አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ከግጭት ነጻና ሰላማዊ ሁኔታዎች መፈጠሩን ገልጸው፥ በቀጣይ የተገኘውን ሰላም ለማጽናት በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሰላም መሆን የማይፈልጉ ኃይሎች መሬት ላይ የሌለ ሃሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ሽብርና ሁከት ለመፍጠር ሲሞክሩ እንደሚስተዋሉ ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ማህበረሰቡ በእነዚህ አካላት ማደናገሪያ መሸበር እንደሌለበት አስገንዝበል፡፡
በአቤል ነዋይ