Fana: At a Speed of Life!

የማህጸን በር ካንሰርን እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመግታት የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የማህጸን በር ካንሰርን እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመግታት በርካታ ሥራዎችን ሠርታለች አለ ጤና ሚኒስቴር፡፡

የጤና ባለሙያዎች ስልጠና፣ የመድኃኒት አቅርቦትን እና ዘርፈ ብዙ ምላሽን በመቅረፍ ረገድ እንደ ሀገር ከፍተኛ ዕድገት እየተመዘገበ መሆኑን በሚኒስቴሩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የአእምሮ ጤና መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት አየለ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ከ14 ሚሊየን በላይ ልጃገረዶች የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እንዲያገኙ ማድጉንም ጠቅሰዋል፡፡

የቅድመ ካንሰር ልየታ/ምርመራና እና ሕክምናን ጨምሮ አጠቃላይ የማህጸን በር ካንሰር መቆጣጠሪያ ስትራቴጂን ተቋማቸው ተግባራዊ ማድረጉን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

ለቅድመ ልየታና ሕክምና የሚውል እንደ ቪዥዋል ኢንስፔክሽን፣ አሴቲክ አሲድ፣ ኤች ፒ ቪ እና ክሪዮቴራፒ ተርማል አብሌሽን የመሳሰሉ ዘዴዎችን በመጠቀም የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ እና ሕክምና አገልግሎት ከ1 ሺህ 500 በላይ በሚልቁ የጤና ተቋማት እንዲሰጥ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግ  የሕክምና ውጤት ከማሻሻሉም በላይ የመኖር ዕድልን ከፍ እንደሚያደርግ አስገንዝበው፤ የጡት ካንሰር መመሪያ እና ማሰልጠኛ ማኑዋል ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል፡፡

የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ልየታ በ226 የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ተቋማት ላይ በማስጀመር፤ ሪፈራል ሊንኬጅ እና ምርመራ እንዲሁም ሕክምና በማጠናከር የጡት ካንሰር ውጤቱን የተሻለ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች ጎን ለጎን በጉዳዩ ላይ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲዘወተሩ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.