በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 8 ሺህ 282 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ይወስዳሉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 8 ሺህ 282 ተማሪዎች ዘንድሮ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ለመውሰድ የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ዳይሬክተር ሸምሰዲን መሐመድ እንዳሉት፤ ከአጠቃላይ ተፈታኞች መካከል 1 ሺህ 253 በኦንላይን ቀሪዎቹ ደግሞ በወረቀት ፈተናቸውን ይወስዳሉ፡፡
የወረቀት ፈተናው በእንጅባራ እና አሶሳ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ኦንላይን ፈተናው በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ይሰጣል ብለዋል፡፡
የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ምትኩ ዘነበ በበኩላቸው፤ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሞዴል ፈተና በወረቀት እና በኦንላይን ለተማሪዎች እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህም ተማሪዎቹን በሥነ-ልቦና ከማዘጋጀት ባለፈ፤ ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ እንዲፈተኑ ይረዳል ነው ያሉት፡፡
በየትምህርት ቤቶቻቸው እና በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጭምር ስለኦንላይን ፈተና አወሳሰድ የክኅሎት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሮቹ የተናገሩት፡፡
በዮሐንስ ደርበው