Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ የሕዝብን ሰላም በመጠበቅ በጋራ መሥራት ይጠበቃል አሉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ ከጤና ባለሙያዎች፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከመምህራን፣ ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮች እና በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቶቹ ዛሬ መጠናቀቃቸውን አስመልክቶ የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኢብራሂም አሕመድ እንዳሉት፤ አቶ አወል ከጤና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የጤና ተቋማትን አቅም በማሳደግና ተደራሽነትን በማስፋት ተገልጋዩን ለማርካት በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች በብቃት የማገልገል ተነሳሽነት ወሳኝ መሆኑንም ርዕሰ መሥተዳድሩ በአጽንዖት ማንሳታቸውን አቶ ኢብራሂም ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ርዕሰ መሥተዳድሩ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት ምክክር፤ በክልሉ የተቀየሱ የልማት ግቦችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የንግዱ ማኅበረሰብ የላቀ ሚናውን እንዲያጠናክር አሳስበዋል ነው ያሉት፡፡

የተጀመረውን የልማት ጉዞ ዕውን ለማድረግ የንግዱ ማኅበረሰብ ሚና የላቀ መሆኑንም አስገንዝበዋል ብለዋል፡፡

ከመምህራንና ከዘርፉ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይትም፤ የትምህርት ስብራቱን በማከም ጥራት ያለው ትምህርት ለትውልዱ ተደራሽ ለማድረግ እንቅፋት  የሆኑ  የግብዓት፣ ክኅሎት፣ አሥተዳደርና ተያያዥ ችግሮች ላይ ጥልቅ ምክክር መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ከሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በውይይቱ የጋራ ትርክቶችን በማጉላት ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር የዘርፉን ሚና ማጎልበት እንደሚጠበቅ ማስገንዘባቸውን አንስተዋል ዳይሬክተሩ፡፡

እንዲሁም ርዕሰ መሥተዳድሩ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እና ተወካዮች ጋር የተወያዩ ሲሆን በዚሁ ወቅትም፤ በትብብር መንፈስ መሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አቶ ኢብራም ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ ለሚደረጉ ምርጫዎች የሕዝብን ሰላም በመጠበቅ እና የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ በጋራ መሥራት እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረሱንም ነው ያስረዱት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.