Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 72 ቢሊየን ብር ብድር ተሰራጨ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪዎች 72 ቢሊየን ብር ብድር ተሰራጭቷል አለ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፡፡

በሚኒስቴሩ የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ አማካሪ አቶ ዳንኤል ኦላኒ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የብድር አቅርቦት ከማሳለጥ አንጻር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ ብልጽግና የማኑፋክቸሪንግ እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ የዘርፉን ምርታማነት ለማጠናከር ከመደበኛ ሥራ በተጨማሪ በንቅናቄ መልክ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዘርፉ የሚስተዋሉ የኃይል፣ የገንዘብ ብድር፣ የመስሪያ ቦታ እና ግብዓት አቅርቦት እንዲሁም ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት በትብብር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለአብነትም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ አንስቶ ሥራ አቁመው የነበሩ እና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በንቅናቄው 72 ቢሊየን ብር ብድር ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ብድር መሰራጨቱን ነው የተናገሩት፡፡

የብድር አቅርቦቱ ኢንዱስትሪዎች ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ እና በተኪ ምርቶች ላይ በስፋት እንዲሰማሩ እድል መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ እስካሁን በዘርፉ በተከናወነ ሥራ ከተኪ ምርቶች 3 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፤ 368 አምራች ኢንዱስትሪዎች አዲስ የኃይል አቅርቦት ማግኘታቸውን እና 83 አዳዲስ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.