ትናንትን ማየት የሚያስፈልገው ለፍርድ አይደለም- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሁል ጊዜም ሰዎች ትናንትን ሲመለከቱ ዛሬ ባሉበት የዕውቀት ልክ፣ ዓለማዊ ሁኔታ እና የሐብት ልክ ከሆነ ሚዛን ይስታሉ ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፉት ሰባት ዓመታት የመንግሥት ሥራ እንቅስቃሴ እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ባደረጉት ልዩ ባለ አራት ክፍል ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል፤ የትናንት ምልከታ እና አረዳድን በተመለከተ አብራርተዋል።
በዚህም፤ ሁል ጊዜም ሰዎች ትናንትን ሲመለከቱ ዛሬ ባሉበት የዕውቀት ልክ፤ ዛሬ ባሉበት ዓለማዊ ሁኔታ እና ዛሬ ባሉበት የሐብት ልክ ከሆነ ሚዛን ይስታሉ፤ ትናንትን ማየት ያለብንም በዚያን ጊዜ በነበረው ዐውድ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ትናንትን ማየት የሚያስፈልገውም ለፍርድ ሳይሆን ለመማር ነው ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በትናንትና ውስጥ ልንማራቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነሱን ካልተማርን ስህተት እንደግማለን፤ ጥፋት እንደግማለን፤ ጥፋት ከደገምን ደግሞ ይያያዝና ለትውልድ ይሻገራል ሲሉ አንስተዋል፡፡
ትናንትን ስናይ ለመፍረድ ከሆነ፤ ያ መደረግ ነበረበት፤ ይህ መደረግ አልነበረበትም ብለን ለመወሰን ከሆነ በዚያ ትውልድ መካከል መገኘት ግድ ይለናል ብለዋል በቃለ መጠይቃቸው፡፡
በትውልዶች መካከል የሐሳብ፣ የዕውቀት እና የሐብት ልዩነት እንዳለ አስገንዝበው፤ ትናንትን ማየት ያለብን ለመማር መሆን አለበት በማለት አስገንዝበዋል፡፡
ምክንያም ከእነ ችግሩም ቢሆን ብዙ ትምህርት ስለሚገኝበት ከእዚያ ውጭ ያለ ዕይታ የተንሸዋረረ ይሆን እና የተሟላ ግንዛቤን እንዳንይዝ ያደርገናል፤ ትናንትን አብዝተን እንጠላለን ወይም አብዝተን እንወዳለን ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም አብዝተን ስንጠላ ልንማር የሚገባንን ነገር እንስታለን፤ አብዝተን ስንወድም ዛሬን መሥራት ሲገባን ያለ ጌዜአችን ትናንት ውስጥ እንኖራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ሁለቱም ትክክል እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ ትናንትን ስንመለከት በራሱ ዐውድ ውስጥ መሆን ይገባል፤ የምንማርበት ነገር እንዳለ እንወቅ፤ ለመፍረድ ሳይሆን ለመማር ትናንትን ማየት ይጠቅማል ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው