በበርካታ ፈተና ውስጥ ሆነንም አስደናቂ ድሎች አስመዝግበናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ሰባት ዓመታት በርካታ ፈተናዎች ገጥመውን የሚያስደንቁ እና ተዓምር ሊባሉ የሚችሉ ድሎች አስመዝግበናል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፉት ሰባት ዓመታት የመንግሥት ሥራ እንቅስቃሴ እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ባደረጉት ልዩ ባለ አራት ክፍል ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል፤ ፈተናዎች እምቅ አቅማችንን ማውጣት አስችለውናል ብለዋል፡፡
በዚህም ከለውጡ በፊት በመከላከያ፣ በደኅንነት፣ በሳይበር ደኅንነት እና ሌሎች ተቋማት ውስጥ የነበረው ብቃት እና ዛሬ ላይ ያለው ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ገልጸው፤ በዚህም ከፍተኛ ብቃት መፍጠር መቻሉን ነው ያረጋገጡት፡፡
አክለውም 130 ሚሊየን ሕዝብ ስላለን ብቻ ሳይሆን ሰልጥነን፣ ተደራጅተን፣ በአዳዲስ ዕውቀት እና ታክቲክ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለመከላከል ያለን አቅም ለውድድር የሚበቃ ጉዳይ አይደለም ነው ያሉት፡፡
እነዚያ ፈተናዎች ባይፈጠሩ ኖሮ በዚህ ልክ እንደራጃለን የሚለውን እጠራጠራለሁ ሲሉ አንስተዋል፡፡
ከለውጡ በኋላ ሰፋፊ የቨርቹዋል ጥቃቶች ሲፈፀሙ እንደነበር አውስተው፤ የሚመጣን ጥቃት የመለየት እና የመከላከል አቅምን በማሳደግ ረገድ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር (ኢንሳ) በኩል ከፍተኛ አቅም ተገንብቷል ብለዋል፡፡
በዚህም በተሟላ መንገድ ሉዓላዊነታችንን ከማንም ኃይል መጠበቅ እንችላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ እንደዚህ አይነት ቁመና የተፈጠረው በፈተና ውስጥም ሆነን ጠንክረን በመሥራታችን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በኮሮና ወቅትም በራችንን ዘግተን በርሃብ ማለቅ የለብንም፤ መሬት ጦሙን ማደር የለበትም በማለት የተጀመረው በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ የማምረት እንቅስቃሴ በእጅጉ ለኢትዮጵያ ማገዙን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት በጣም በርካታ ፈተናዎች ገጥመውን ለማመን የሚያስደንቁ እና ተዓምር ሊባሉ የሚችሉ ድሎች ማስመዝገብ ችለናል ነው ያሉት በቃለ መጠይቃቸው፡፡
በዮናስ ጌትነት