ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጀምረን ያልጨረስነው ፕሮጀክት የለም አሉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን የብልጽግና መሠረት እስከምንጥል ድረስ ትጋቱም ውጤቱም ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፉት ሰባት ዓመታት የመንግሥት ሥራ እንቅስቃሴ እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ባደረጉት ልዩ ባለ አራት ክፍል ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል፤ ሳንተጋ እና ሳንለፋ ከፈለግነው መዳረሻ መድረስ እንደማይቻል እና የአቋራጭ መንገድ የምንፈልገውን ውጤት ሊያመጣልን እንደማይችል እንገነዘባልን ብለዋል፡፡
በተለመደው አሠራር መሪዎች ከቢሮ ስለማይወጡ እና ጉዳዩን በዓይናቸው ስለማያዩ በርካታ የውሸት ሪፖትርቶች እንደሚቀርቡ አንስተዋል፡፡
በአንጻሩ ሥራውን እያዩ የሚመሩ ቁርጠኛ አመራሮች ባሉበት አካባቢ ተግባራት በፍጥነት ይከወናሉ ነው ያሉት፡፡
በዚህም ወደ መሬት ወርደን ሥራዎችን በአካል እየተከታተልን ስንሠራ በርካታ ትምህር ይገኝበታል፤ አድካሚ ቢሆንም ለሰዎች ጉልበት ሰጪ ክትትል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዚህ መልኩ ጀምረን፣ አስበን፣ ያልጨረስነው ፕሮጀክት የለም ነው ያሉት፡፡
የማይመስሉ እና በእኛ አቅም የማይታሰቡ ጉዳዮች እናስባለን ነገር ግን ስለሚመሩ እና ክትትል ስለሚደረግባቸው ይጠናቀቃሉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡
አሁንም ኢትዮጵያን ለማበልጸግ መሰረት እንጥላለን ብለን ቃል የገባነውን ነገር ያለምንም ጥርጥር እናደርገዋለን በማለት አረጋግጠዋል፡፡
ሐሳቡ አለን፣ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን ለመከወን የሚያስችል ትጋቱ አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሕዝባችንን ይዘን የኢትዮጵያን የብልጽግና መሰረት እስከምንጥል ድረስ ትጋቱም ውጤቱም ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
በዮናስ ጌትነት