ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር እንዲገቡ መደረጉ ያተረፍንበት ውሳኔ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በለውጡ ማግስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር እንዲገቡ መደረጉ ያተረፍንበት ውሳኔ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ያለፉት ሰባት ዓመታት የመንግሥት ሥራ እንቅስቃሴ እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ባደረጉት ልዩ ባለ አራት ክፍል ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል፤ በለውጡ ማግስት የተወሰነውን የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር እንዲገቡ መደረግን በተመለከተ አብራርተዋል፡፡
በለውጡ የተቀበልናት ኢትዮጵያ በበርካታ ችግሮች ውስጥ ነበረች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለአብነትም ለሠራተኞች ደመወዝ መክፈል የማይቻልበት፣ 59 በመቶ አጠቃላይ ሀገራዊ ዕዳ የነበረባት፣ በመሬት አቀማመጥ እስረኛ የሆነች፣ የተቋም ድቀት የነበረባት እና በርካታ አሳሪ ሕጎች እንዲሁም ከፋፋይና በታኝ ትርክት የተስፋፋባት ነበረች ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የሚድያ እና የፖለቲካ ዐውዱ የተሳከረ እንደነበረ አውስተው፤ በወቅቱ የነበረው ጥያቄ “እንፈርሳለን አንፈርስም” የሚል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ ያለ ሀገርን የሚመራ መንግሥት ጠንከር ያለ ፈታኝ ውሳኔዎችን መወሰን እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል፡፡
ውሳኔዎቹ ሙሉ በሙሉ መልካም ግብረ መልስ ይኖራቸዋል ማለት ባይሆንም መደረግ ያለበት ጥቅሙን ማጉላት እና ጉዳቱን መቀነስ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
በመሆኑም በነበረው ዐውድ ሚዲያውን፣ የፖለቲካ ሁኔታውን፣ የተቋማት ግንባታውን፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር እንዲገቡ፣ እስረኞች እንዲፈቱ በመወሰን የፖለቲካ ሁኔታውን ለመቀየር መሠራቱን ነው ያስረዱት፡፡
የተፈታው እስረኛ ሁሉ ለሀገር ጠቃሚ ነው፤ ወንጀል ሳይሠራ ጥፋት ሳያጠፋ ነው የታሰረው ብለን ሳይሆን ከነበረው የተቋም ስብራት አንፃር ይህንን ለመለየት የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ ነው ብለዋል።
በዚያ ምክንያት መልካሙን ከክፉው ደምሮ በጊዜ ሂደት እየጠራ እንዲሄድ መወሰን እንደነበረበት ነው ያስገነዘቡት፡፡
እኛ ስንመጣ መጀመሪያ ቃል የገባነው ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ማምጣት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ሁሉንም አካላት እንዳይገቡ ብንከላክል የምናስበውን ዴሞክራሲ ልናመጣ አንችልም ነበር ብለዋል።
የእኛ ውሳኔ የነበረው ሁሉም መድረክ እንዲያገኝ፣ ሁሉም ሐሳቡ ተደምጦ እና ተመዝኖ በሕዝብ እንዲወሰን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አክለውም በአጠቃላይ በውሳኔው አትርፈንበታል፤ የተጎዳንባቸው አካባቢዎች አሉ እነርሱን እየተማርን እና እየቀነስን ጥቅሙን እያጎላን እንቀጥላለን ብለዋል በክፍል አንድ ቃለ መጠይቃቸው፡፡
በዮናስ ጌትነት