ቀጣናዊ ልማትን ለማሳደግ በትብብር መስራት አስፈላጊ ነው – አቶ አሕመድ ሺዴ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ኬንያን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ያለመ የምስራቅ አፍሪካ የልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ በዚህ ወቅት÷ የቀጣናው ሀገራት የንግድ ትብብርን ማጠናከር የሚችሉ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ቀጣናዊ ትስስርን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አንስተዋል።
በተለይም የቀጣናው ሀገራት የጉምሩክ አሰራርን በማሻሻል ለንግድ ስራ ተስማሚ የሆነ የድንበር አካባቢ ሊፈጥሩ እንደሚገባ ገልጸው÷ ኢትዮጵያም የጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የድንበር አካባቢ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
የኬንያ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስረውን የሱፍቱ እና ራህሙ ድልድዮች ለመገንባት ቃል መግባቱን ያደነቁት ሚኒስትሩ÷ ይህም የሁለቱን ሀገራት የልማት ራዕይ የሚያፋጥን ነው ብለዋል።
ከመንገድ መሰረተ ልማቶች ትስስር በተጨማሪ ሁለቱ ሀገራት በጋራ የትብብር ማዕቀፍ በቴክኖሎጂ ልማት ዘርፎችም በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የዓለም ባንክ እና ኢጋድ ላደረጉት የፋይናንስ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
በየሻምበል ምህረት