Fana: At a Speed of Life!

የስሎቬኒያ መንግስት ለኢትዮጵያ በግብርናው መስክ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል – ፕሬዚዳንት ፒርክ ሙሳር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የስሎቬኒያ ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር በአዲስ አበባ የሚገኘውን ዘመናዊ የንብ ማነቢያ ሰርቶ ማሳያን መርቀው ከፍተዋል።

ኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት የያዘችውን ግብ ለማሳካት ያስችላል የተባለውንና የጥራት ደረጃ የጠበቀ የማር ምርት ለማግኘት የሚያስችል ዘመናዊ የንብ ማነቢያ ሠርቶ ማሳያ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን ዕምቅ ሀብት በምርምር በመደገፍ የሌማት ትሩፋት ግቦችን ቀድሞ ማሳካት እንደሚቻል ገልጸዋል።

የተጀመረው የንብ ማነቢያ ሠርቶ ማሳያ ምርታማነትን በማሳደግ የተሻለ ህይወት ለመምራት እንደሚያስችልም አንስተዋል።

ስሎቬኒያ በንብ ማነብ በዓለም ላይ ከፍተኛ ስም እንዳላት ጠቅሰው÷ በዚህና በሌሎች ዘርፎች በትብብር እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

ፕሬዚዳንቷ ሀገራቸው ስሎቬኒያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በማር ምርት የሌማት ትሩፋት ግቧን ቀድማ ማሳካት የሚያስችላትን በምርምር የተደገፈ የንብ ማነብ ቴክኖሎጂና የማር ምርት ማግኘት እንደምትችል ጠቁመዋል።

መንግስት ባለፉት ዓመታት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አበክሮ እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት ፡፡

በመዲናዋ ወደ ተግባር የገባው ዘመናዊ የንብ ማነቢያ ሰርቶ ማሳያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ ርምጃ መሆኑን ገልጸው÷ ብዝሃ ህይወትን በመንከባከብ እና ለማህበረሰቡ የትምህርት ምንጭ ሆኖ በማገልገል ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለውም አስገንዝበዋል።

በግዛቸው ግርማዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.