Fana: At a Speed of Life!

ሴት ሐጅ አድራጊዎች: ከኢትዮጵያ እስከ መካ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሐጅ ከእስልምና ምሶሶዎች አንዱ ነው። በመሆኑም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ በዘር፣ በቀለም፣ በቋንቋ እና በጾታ ሳይለይ ሐጅ ማድረግን ያልማሉ። ህልማቸው ሲሳካም ከዓለም ማዕዘናት ወደ አንድ አቅጣጫ በመትመም «ለበይክ አላሁመ ለበይክ፤ ለበይክ አላሁመ ለበይክ … » እያሉ ይገናኛሉ።

በዚህም ስፍራ የእምነትን ድምጽ ይጎላል፤ ነፍያም እጅግ ሐሴት ታደርጋለች።

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ሐጅ ለማድረግ ለዓመታት ሳይታክቱ ጥሪት ይቋጥራሉ። በዚህ ረገድ ሴት ሙስሊሞችም ‘መካ’ ለመድረስ አልመው ብዙ ለፍተው ህልማቸውን እውን የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው።

ከህልማቸው ለመድረስ ጥሪት ለመቋጠር ቀን ከሌት ለፍተው ላባቸውን ጠብ አድርገው ይሰራሉ። የቤታቸውን ጓዳ ከመሙላት ጎን ለጎን ለሐጅ ህልማቸው መሳካት ይተጋሉ።

ይሄ የብዙ ሁጃጅ ሴቶች ታሪክ ነው። ግብርና እና ንግድን ጨምሮ በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰማርተው በትጋት ሰርተው ካሰቡት ይደርሳሉ።

ከገጠር ተነስተው እስከ አዲስ አበባ፤ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ መካ ድረስ ተጉዘው የልባቸውን መሻት የሞሉ ሴት ሁጃጆች ብዙ ናቸው።

አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሐጅ አድራጊዎች ለዚህ ክብር የደረሱበትን መንገድ ሲተርኩ ትዕግስት እና ትጋትን እናነባለን። ሐጅ ለማድረግ ከ15 ዓመታት በላይ የቆጠቡ ሴቶች መኖራቸውን መስማት እንግዳ አይሆንም።

ከዚህም በላይ የልባቸውን መሻት ይሞሉ ዘንድ ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ያለ እረፍት መሥራታቸው ይደንቃል።

አንዲት እናት “ለ15 አመታት ገንዘብ በአነስተኛ ሳጥን አስቀምጥ ነበር። ገንዘቡንም እያጠራቀምኩ አንድ ቀን ሐጅ ማድረግ እንደሚሳካልኝ አስብ ነበር” ብለዋል።

አሁን ሐጃቸው ሞልቶ ወደ መካ አቅንተዋል፤ የእኚህን እናት ታሪክ ብዙዎቹ ሐጅ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ይጋሩታል።

ለሐጅ ህልማቸው ጥሪቱ ሞልቶላቸው አዲስ አበባ መድረስ እንዲሁም ከአዲስ አበባ መካ መጓዝ አልጋ በአልጋ አይሆንላቸውም። የመንገድ እንግልት፣ አረብኛ ወይም እንግሊዘኛ ቋንቋ አለመቻል የሁጃጆቹ ፈተና ይሆናሉ።

ይህም ቢሆን ግን በበጎ ፈቃደኞች ድጋፍ እና ሌሎች የሐጅ ተጓዦችን በጥንቃቄ በመመልከት የአምልኮ ሥርዓቱን ፈጽመው ይመለሳሉ።

ምንም እንኳ ጉዟቸው ውጣ ውረድ የበዛበት ቢሆንም መካ በደረሱበት ቅፅበት ድካሙ ሁሉ ይጠፋል። ተጓዦች ለመጀመሪያ ጊዜ ካዕባን ሲመለከቱ አይናቸው በእንባ ይሞላሉ። አንዲት ሐጅ አድራጊ ይህንን ቅጽበት “ሱጁድ አድርጌ (እየሰገድኩኝ) ባልነሳ ተመኘሁኝ:: መድረሴንም ማመን አቃተኝ:: በፎቶ ብቻ ከማውቀው ካዕባ ደርሻለሁ አላህ የተመሰገነ ይሁን” ብለዋል።

በጣም የሚያስደንቀው በካዕባ በርከት ያሉ አረጋውያን ሴቶች የሚደርሱ ሲሆን አንዳንዶቹ ከበድ ያለ የጤና እክል ቢኖርባቸውም የአምልኮ ሥርዓቶችን በሙሉ ያጠናቅቃሉ።

በዚህም በትዕግስትና በቆራጥነት ሐጅ አድርገው ከእስልምና ምሶሶዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን ያሟላሉ። የመንፈሳዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትግል ሕይወት ፍጻሜ እና ውስን ሀብቶች ቢኖሩም የእውነተኛ እምነት መግለጫ ነው። ድህነት፣ ርቀት ወይም ህመም የመጨረሻ ግቧን ከማሳካት የማይከለክላትን ታማኝ ሴት ህያው ምሳሌን ይወክላሉ።

በኑርሁሴን አብዱልሃፊዝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.