የንግድ ሚዲያዎች ትውልድ ገንቢ ሃሳቦችና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የንግድ ሚዲያዎች ትውልድ ገንቢ እና መልካም አመለካከት የሚቀርጹ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል አለ።
መንግሥትና የንግድ ሚዲያዎች በሀገር ግንባታ ሥራዎች ላይ ይበልጥ ተቀራርበው መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ በዚህ ወቅት፥ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የተገኙ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አብራርተዋል።
በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በዲፕሎማሲ መስኮች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው÷ መገናኛ ብዙሃንም የተመዘገቡ ስኬቶች ላይ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ በኩል የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና መጫወታቸውን አመልክተዋል።
ከንግድ ሚዲያዎች አኳያ ተመልካች ለማግኘት ሲባል አንድን ጉዳይ የማስጮህ፣ አውድን ያልተረዳ ዘገባን የማሰራጨት፣ በጥናት ላይ ያልተመሰረተ እና የችኮላ አዘጋገብ እንደሚስተዋል አንስተዋል፡፡
ሀገራዊ አጀንዳዎች የፓርቲ ወይም የመንግሥት ብቻ አድርጎ የማሰብ እና በቸልተኝነት የማለፍ አዝማሚያ መኖሩንም ነው ያብራሩት፡፡
ብሔራዊ ጥቅምን ጨምሮ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራና በተናበበ መልኩ በአግባቡ መስራት ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው÷ መገናኛ ብዙሃን ትውልድ ገንቢ እና መልካም አመለካከት የሚቀርጹ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።
መንግስት መረጃ የማግኘት ነጻነት መረጋገጥ እንዳለበት ሙሉ እምነት እንዳለው ገልጸው ÷ ክፍተቱን በዘላቂነት ለመፍታት በመንግሥት በኩል ዝግጁነት መኖሩን አረጋግጠዋል።
አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎች ከአንድ ሥርዓት ጋር የሚያያዙ ሳይሆኑ ለትውልዱ የሚሻገሩ በመሆናቸው የንግድ ሚዲያዎች አጀንዳ አድርገው ሊዘግቡባቸው እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ የአቅም ግንባታ መሆኑን እና ለዚህም ባለስልጣኑ የባለሞያዎችን አቅም በማዳበር በሀገራዊ ጉዳዮች የጋራ አቋም ለመያዝና ተቀራርቦ ለመስራትየሚያግዝ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመገናኛ ብዙሃኑ የሚስተዋሉ ስሜት ተኮር የአዘጋገብ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚያስችል አመልክተው÷ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በጥልቀት የመዘገብ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ባለስልጣኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።