በትጥቅ ትግል የስልጣን ፍላጎትን ማሳካት የሚቻልበት ጊዜ አብቅቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትጥቅ ትግል የፖለቲካ ስልጣን ፍላጎትን ማሳካት የሚቻልበት ጊዜ አብቅቷል አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ባለ አራት ክፍል ቃለ ምልልስ በክፍል አራት÷ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ግጭቶችና በሃይል ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረጉ ሙከራዎች ዋነኛ መንስኤያቸው የፖለቲከኞች ከፍተኛ የስልጣን ጥማት እና የተሳሳተ ትርክት ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ ሃይሎች ከምርጫ እና ከሕዝብ ይሁንታ ይልቅ ስልጣን የሚገኘው በመሳሪያ ብቻ ነው ወይም ደግሞ ስልጣን ስልጣን የሚሆነው እኔ ከመራሁ ብቻ ነው ብለው የሚያስቡ ናቸው ብለዋል፡፡
የለውጡ ሃይሎች ብዙ ፈተና ቢደርስባቸውም ከትጥቅ ትግል ይልቅ ሰላማዊ አማራጭን ቅድሚያ በመስጠት እና ውስጣዊ ፖለቲካ ማሻሻያ በማድረግ ለውጡን እውን ማድረግ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
በትጥቅ ትግል ሀሳብን ማሳካት የሚቻልበት ጊዜ አብቅቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ በግጭት የሚሳተፉ ሃይሎች ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስት ለሰላም ሁሌም በሩ ክፍት መሆኑን ጠቅሰው ÷የፕሪቶሪያውን ስምምነት ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ አሳይቷል ብለዋል፡፡
መንግስት አካታቸ የፖለቲካ ሥነ ምህዳር ለመፍጠር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቀሙን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ በዚህም ዜጎች መስተካከል አለባቸው ያሏቸውን ሀሳቦች ለኮሚሽኑ እያስረከቡ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ይህም እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያግዝ ነው አጽንኦት ሰጥተው ያብራሩት፡፡
ስልጣን ሀሳብን በመሸጥ በሕዝብ ዘንድ ሲገዛ የሚገኝ ነው ፤ በትጥቅ ትግል እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሃይሎች ወደ ሰላም አማራጭ በመምጣትና በፓርቲ በመደራጀት ሃሳባቸውን ማሳካት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉበት እንጂ አንዱ አንዱን የሚገዛበት ሥርዓት የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ከመገዳደል እና መጠላለፍ መውጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ