Fana: At a Speed of Life!

የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት በቀጣይ ዓመታት የሚኖረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያ ማዕከል ያደረገ ነው – አቶ አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት በቀጣይ ዓመታት የሚኖረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያ ማዕከል ያደረገ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

አቶ አሕመድ ሺዴ የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸምና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የመንግስት የፕሮጀክቶች አፈጻጸም በፍጥነትና በጥራት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በመንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዘርፍ አመርቂ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው÷ በአሁኑ ወቅት ከ22 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመስኖ ልማት ረገድም የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡንና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች በታለመላቸው ጊዜና ጥራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ በዚህም በርካቶቹ ተጠናቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን ነው የገለጹት፡፡

የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ መወሰን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከፖሊሲ ጋር የተገናኙ የኮትሮባንድ ግፊቶች በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ማሻሻያውን ተክትሎም በወርቅ ግብይት ላይ የነበረው የኮትሮባንድ ችግር መፈታቱን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር የምታደርገው የንግድ ግንኙነት፣ የመሠረተ ልማት ትስስርና የኢነርጂ አቅርቦት ተጠናክረው መቀጠላቸውንም አብራርተዋል፡፡

የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት በቀጣይ ዓመታት የሚኖረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያ ማዕከል ያደረገ፣ የመንግስትን የገቢ አቅም በመተንበይ፣ የሚኖሩ ሌሎች ገቢዎችን ታሳቢ በማድረግ እና የመንግስትን የወጪ ፍላጎት በመተንተን የተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በጀቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል፣ ማህበራዊ ድጎማዎችን እና የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚን ከማስቀጠል አንጻር ብሎም ሌሎች ተግባራትን በውጤታማነት ከማከናወን አኳያ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁሉም አመልካቾች አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ መገልጻቸው ይታወቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.