የፓርኮችን ደኅንነት በመጠበቅ የቱሪዝም ዘርፉን ልናሳድግ ይገባል – አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፓርኮችን ደኅንነት በመጠበቅ የቱሪዝም ዘርፉን ልናሳድግ ይገባል አሉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ።
የተለያዩ የውጭ ሀገራት ኢንቨስተሮች ከአቶ ኃይለማሪያም ጋር በመሆን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘውን የማዜ ብሔራዊ ፓርክ ጎብኝተዋል።
አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በጉብኝቱ ወቅት÷ ፓርኩ የልዩ ልዩ ብዝሃ ሀብት መገኛ መሆኑን አንስተው፤ ጥበቃውን በማጠናከር ለቱሪዝም ዘርፍ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የተጀመረው ፓርኩን ማዕከል ያደረገ የኮሪደር ልማት ስራ በጎ ጅምር እንደሆነና የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን በሥራው የራሱን አሻራ እንደሚያሳርፍ ገልጸዋል።
በዚህም ፋውንዴሽኑ የፓርኩ መሠረተ ልማትን ማሟላት፣ ስካውቶቹ ሳይቸገሩ የጥበቃና ቁጥጥር ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የመኪና፣ የመገናኛ ሬዲዮና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባሕል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይኒቱ መልኩ÷ ፓርክ በ202 ስኩዌር ኪሎሜትር በሚሸፍን ቦታ አንበሳን ጨምሮ የበርካታ ዱር እንስሳት መኖሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርኩን የመጠበቅና የማስተዋወቅ ሥራ በመሥራት በሚያገኘው ገቢ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ወደሚችልበት ደረጃ ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በመለሰ ታደለ