ሴቶች ለሀገርና ለትውልድ ግንባታ ሚናቸው ከፍተኛ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሴቶች ለሀገርና ለትውልድ ግንባታ ሚናቸው ከፍተኛ ነው አሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማ አቀፍ የሴቶች የማጠቃለያ ውይይት “የሴቶች ሚና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሐሳብ ተካሂዷል።
በመድረኩ ከመዲናዋ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተወከሉ ሴቶች አስተያየት እና ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማትና የተማሪዎች ምገባን ጨምሮ የዜጎችን በተለይም የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋገጡ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን አድንቀው÷ ይህም እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ትልቅ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁሉም የልማት ስራ ውስጥ ደግሞ የሴቶች ተሳታፊነት ጎልቶ የሚታይ በመሆኑ ይበልጥ የሚያስደስት ነው ብለዋል።
ተወያዮቹ በመድረኩ ላይ ከኑሮ ውድነት፣ ከመኖሪያ ቤት ችግር፣ የሥራ ዕድል እንዲሁም ከጤና መድህን ጋር ተያይዞ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገርም ሆነ በመዲናዋ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አብራርተዋል።
ከፊታችን ያለው ጊዜ ብሩ ተስፋ የሞላበት በእምነት የነገውን ብልጽግና ለማሳካት የምንጥርበትና ስንቅ የምሰንቅበትና ነው ያሉት ከንቲባዋ÷ በዚህም ሴቶች ለሀገራቸው ጉዳይ የጀርባ አጥንት ናቸው ብለዋል።
ይህን ለማጠናከርና ሴቶች ከሐሳብ ጀምሮ እስከ ተግባር በልማት እንዲሳተፉ እና ለቀጣይ በጀት ዓመት ስራ ግብአት ለማሰባሰብ መድረኩ መዘጋጀቱን አንስተዋል።
የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያን ጨምሮ የገበያ ማእከላት እንደሚስፋፉ እና በቅርቡም ሁለት የገበያ ማእከላት ተመርቀው ለህዝብ ክፍት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የቤት ችግርን ለመቅረፍም የተለያዩ አማራጮች እየቀረቡ መሆኑን አንስተው÷ ሌሎች የተነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንደሚሰራ እና እየተሰራ እንደሚገኝ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
በተለይም በሚቀጥለው ዓመት የመጠጥ ውሃና የቤት አቅርቦት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያነሱት።
በሌላ በኩል ሴቶች እንደ ሁልጊዜው ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ እና ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በፌቨን ቢሻው