ለክልሎች በሚተላለፈው የጋራ ገቢዎች ፍትሃዊ የበጀት ሥርጭት ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል – አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር
አዲስአበባ፣ ሰኔ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ለክልሎች የሚተላለፈው የጋራ ገቢዎች የበጀት ሥርጭትን ፍትሃዊ ለማድረግ በተሰራ ሥራ ተጨባጭ ለውጥ ጥቷል አሉ።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተዘጋጀው ውስን ዓላማ ባላቸው የድጎማ በጀቶች ትልልፍና በጋራ ገቢዎች ክፍፍል ላይ ያተኮረ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር÷ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በክልሎች መካከል ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ለመፍጠር የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ከሀገራዊ ለውጡ በፊት አራት ቢሊየን ብር የነበረው የክልሎች የጋራ ገቢ የበጀት ክፍፍል አሁን ላይ ከ70 ቢሊየን ብር በላይ መድረሱን አንስተዋል።
የድጎማ በጀት ስርጭትን ግልፅና ፍትሃዊ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸውንና በዚህም ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን አብራርተዋል።
በውስን ዓላማ ባላቸው ድጎማዎች የአሰራር ግልጽነትና የአተገባበር ክፍተት ላይ የሚነሱ ውስንነቶችን ለመፍታት የዳሰሳ ጥናት መካሄዱንም አመልክተዋል።
የክልል መንግስታት ከፌዴራል መንግስት ስለሚደረግላቸው ድጎማ ለሚመለከታቸው ተቋማት በግልፅ ማሳወቅ እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡