Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ8 ሚሊየን በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ በክልሉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 8 ሚሊየን 400 ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ አለ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዘላለም አረጋ ለፋና ዲጅታል እንደገለጹት፤ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ያስገኛል።

በክልሉ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በዋነኛነት የሚሳተፈው ወጣቱ የማህበረሰብ ክፍል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከአጠቃላይ ቁጥሩ ከ65 በመቶ በላይ እንደሚሸፍን ጠቁመዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ፣ የአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ቤቶችን ማደስና መስራት፣ የግብርና፣ የትምህርት እና የጤና ዘርፎችን ጨምሮ በ14 ዋና ዋና የሥራ መስኮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከ13 ሚሊየን በላይ የሚሆን ህብረተሰብ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆን ያመለከቱት ምክትል ኃላፊው፤ በዚህም 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ማዳን የሚያስችል ተግባር ይከናወናል ብለዋል።

ዕቅዱ ተግባራዊ ሆኖ ግቡን መምታት የሚችለው ሁሉም ባለድርሻ የበኩሉን ሲወጣ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች እንደተለመደው በትጋት እና በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.