ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ለማስተዋወቅ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መጠቀም ይገባል – አቶ አህመድ ሺዴ
አዲስአበባ፣ ሰኔ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለውጭ ኢንቨስትመንት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መጠቀም ይገባል አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ።
የውጭጉዳይ ሚኒስቴር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ በቂ ግንዛቤ የሚያገኝበት መመሪያ ዛሬ ይፋ አድርጓል።
አቶ አህመድ ሺዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።
በተለይም በ2ኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲወሰን በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጨመሩን አንስተዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው የዲፕሎማሲ መመሪያ ሰነድም የኢንቨስትመን ፍሰትን በመጨመር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ያስመዘገበችውን ውጤት ለማላቅ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው÷ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግም ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን መተግበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ በኢኮኖሚ ማሻሻያው በግብርና ዘርፍ በስንዴ ምርት እንዲሁም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሻሻልና ተኪ ምርቶችን በማምረት ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የዕዳ ጫናዋን በመቀነስ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ከሚያስመዘግቡ ሀገራት ተርታ መመደቧን አስታውሰው ÷ ቀጣይነት እንዲኖረው የኢትዮጵያን አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮች በሚገባ ማስተዋወቅ ይገባል ነው ያሉት።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታና ምቹ የኢንቨስትመንት አቅም በተዘጋጀው መመሪያ ሰነድ አማካኝነት ማስተዋወቅ ይኖርባቸዋል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡