Fana: At a Speed of Life!

ከ1 ሚሊየን በላይ የልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ወደ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ተሸጋገሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ450 ሚሊየን ዶላር እየተተገበረ በሚገኘው የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከ1 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች ወደ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ተሸጋግረዋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ከተረጅነት ወደ ምርታማነት የማሸጋገር ስራ ውጤታማ እየሆነ ነው ብሏል።

የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በ88 ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን በሚኒስቴሩ የከተማ ምግብ ዋስትና ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ብርሀኑ ተሾመ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ በ2009 ዓ.ም ከተጀመረ ወዲህ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ከ1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ወደ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ እንዲሸጋገሩ አስችሏል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት፥ በዚህ አመት ብቻ ከ690 ሺህ በላይ ዜጎች በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከነዚህም ውስጥ ከ500 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች ከተረጅነት ወጥተው ራሳቸውን ወደመቻል ተሸጋግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ ሰርቶ የመለወጥና የቁጠባ ባህልን ማሳደግና ልማታዊ ስራዎችን መከወን ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ባለፉት 10 ወራት ብቻ ከ600 ሚሊየን ብር በላይ መቆጠብ መቻላቸውንም ነው አቶ ብርሃኑ የገለጹት፡፡

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.