Fana: At a Speed of Life!

የትምህርት ጥራት በመንግስት ፖሊሲ ብቻ አይመለስም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የትምህርት ጥራት በመንግስት ፖሊሲ ብቻ የሚመለስ ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከመላው ሀገሪቱ ከተውጣጡ የመምህራን ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፥ የጋራ ትርክት እንደሚያስፈልግ አውቀን ዕቅድ አውጥተን እና ስትራቴጂ ቀይሰን እየሰራን ነው ብለዋል።

ለዚህም የመምህራን ድጋፍ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፤ የጋራ ትርክትን በተመለከተ ሚዲያውን ጨምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቢነገርም መምህራን በየትምህርት ተቋማቱ ትውልዱን በሚገባ ማስረዳት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሩን ማስተማር እና ማንቃት ላይ አብራችሁን ልትሰሩ ይገባል ያሉ ሲሆን ይህንን ካደረጋችሁ ብዙ ለውጦችን ማምጣት እንችላለን ብለዋል።

በጋራ መስራት ከተቻለ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ እንደሚቻልም አመላክተዋል።

መምህራን የሁሉም አስተማሪ እንደመሆናችሁ በቀበሌ እና ወረዳ ላይ የሚረብሸውን እናንተው ስላስተማራችሁት ህዝብህን አገልግል፣ ታሪካችን እና ባህላችን አይፈቅድም እያላችሁ ብታስተምሩ ብዙ ሰው ይለወጣል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

እንደነዚህ ያሉ ጉዳዮችን መንግስት ብቻውን ሊፈታው ስለማይችል በጋራ ብንሰራ እና ብንተጋገዝ መልካም ነው ብለዋል፡፡

የእኛን ሁኔታ በመገንዘብ እና ብዙ ዕዳ ያለባት ሀገር መሆኗን አውቀን ቀን ከሌት ሰርተን በፍጥነት እንለወጥ ካላችሁ መተጋገዝ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ፖሊሲዎቻችንን እንፈትሻለን ነገር ግን አንዳንድ ጉዳዮች ላይ በጋራ ካልሰራን የማይመለሱ ጉዳዮች ስላሉ ካገዛችሁን ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ እንጂ በርግጠኝነት የማይፈታ ችግር አይኖርም ብለዋል።

መንግስት ችግሮችን ለመፍታት ለውይይት እና ለምክክር በሩ ክፍት መሆኑን አንስተው፤ ይህ እንዲሳካ ግን መምህራን የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.