Fana: At a Speed of Life!

መምህራን የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በሒደት ለመፍታት በትኩረት እንሰራለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መምህራን የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በሒደት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በትኩረት እንሰራለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመላው ኢትዮጵያ ከተወጣጡ መምህራን ጋር ባካሄዱት ውይይት ላይ እንዳሉት÷ በእውነትና እውቀት የተገነባ ትውልድ ለመፍጠር የመምህራን ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

መምህራን ለሀገር ግንባታ አስፈላጊ መሆናቸውን እናምናለን በማለት ገልጸው÷ ለዚህም የለውጡ መንግስት በፓርላማ ፊት ለመምህራን እውቅና መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡

የመምህራን ዋና ተልዕኮ ትውልድ ለመፍጠር መስራትና መድከም በመሆኑ ዋጋቸው በደመወዝ እንደማይተመን አስረድተዋል፡፡

እውቀትና እውነት መስፈሪያ እንዲሆኑ መምህራን በትኩረት መስራት አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ እውነት እና እውቀት ፈታኝ እና ዋጋ እንደሚያስከፍሉም አብራርተዋል፡፡

አሁን ያለንበትን ዘመን በቅጡ መረዳት እንደሚገባ አንስተው÷ ዘመኑን ካልተረዳን ደግሞ ትውልድ ማስቀጠል አንችልም ነው ያሉት፡፡

ያለንበት ዘመን ውሸትና ጩኸት የነገሰበት ነው፤ ውሸትና ጩኸት ደግሞ የተሰራን ያፈርሳሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የድህረ እውነት ዓላማ ከዕለት ጉርስ ተሻግሮ ማሰብ የማይችል ትውልድ መፍጠር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በድህረ እውነት ዘመን መምህራን እውነትና እውቀትን የማጣራት መሰረት ሊሆኑ እንደሚገባ አንስተው÷ ለዚህም ካለፈ ታሪክ ተገቢውን ትምህርት መውሰድ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ዘረኝነት በብሔር ብቻ ሳይሆን በየሰፈሩ መንሰራፋቱን አብራርተው÷ ሁሉንም ልዩነቶች በመቀበል አንድ በሚያደርጉን ጥላ ሥር ሀገር መስራት አለብን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የተረከብነው ሀገር እዳ፣ ድህነት፣ ችግር ያለበት እና አንድነቱ የላላ ነው፤ ይሄን ደጋግመን ብናወራ ለውጥ የለውም፤ ከዚህ መውጣት የሚያስችል ራዕይና ትጋት ግን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ችግርን እያየን መካድ እና መሸሽ ሳይሆን በመጋፈጥ ተቸግረንም ቢሆን ሀገሪቱን ካለችበት አረንቋ ለማውጣት እንችላልን የሚል እምነት መምህራን መያዝ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

መምህራን ያለውን ችግር እና እድል በቅጡ ሊረዱ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ለዚህም የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉና ለልጆቻችን የተሻለች ኢትዮጵያን ለማውረስ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የመምህራን ጥያቄዎች ከሌሎች ዘርፎች የሀገሪቱ ሠራተኞች ጋር በማሰናሰል በፖሊሲ ማዕቀፍ በሒደት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

ለመምህራን ብቻ በልዩ ሁኔታ የደመወዝ ጭማሪ ብናደርግ ችግሩ አይፈታም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የመምህራን ችግር በደመወዝ ጭማሪ ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን መገንዝብ ይገባል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.