የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ የ2018 ዓ.ም በጀት 350 ቢሊየን ብር እንዲሆን ወሰነ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የ2018 ዓ.ም በጀት 350 ቢሊየን ብር ሆኖ ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ባካሄደው 4ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ስብሰባ በሁለት ወሳኝ ከተማ አቀፍ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚህ መሰረትም ካቢኔው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም በጀት 350 ቢሊየን ብር ሆኖ ለምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ አሳልፏል።
ከረቂቅ በጀቱ 249 ነጥብ 9 የሚሆነው በዋናነት ድህነት ቅነሳ ፣ ለዘላቂ ልማት፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ ለመሰረተ ልማት እና ሌሎች ትላለቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንዲሁም ለአገልግሎት እና አቅርቦች ድጎማዎች እንደሚውል ተመላክቷል፡፡
ቀሪው 100 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ቁጠባን መሰረት ላደረገ የመደበኛ በጀት ጣሪያ የሚመደብ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም ካቢኔው በመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ተጠንቶ በቀረበው የመሬት ወቅታዊ የሊዝ ጨረታ ዋጋ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚህም በኮሪደር ልማት በለሙ አካባቢዎች የመሠረተ ልማት አቅርቦት ደረጃ ከፍ በማለቱ እና የኮሪደር ልማቱ በከተማ ውስጥ የነበረውን የመሬት ዋጋ ከመረጋጋት አንጻር እና የቀጣይ የከተማዋን የመልማት ፍላጎት በማጥናት የቀረበውን የመሬት ሊዝ ዋጋ ማሻሻያ ማጽደቁን የከተማው ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡