በጥበብ ብሶትን ሳይሆን ቁጭትና ተስፋን ለማሳየት መስራት ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በጥበብ ሥራቸው ብሶትን ሳይሆን ቁጭት እና ተስፋን ለማሳየት መስራት አለባቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ከተወጣጡ የጥበቡ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ ጥበብ የአንድን ሕዝብ ባህል፣ እሴትና ሁለንተናዊ ማንነት ለማሳየት ጉልህ ሚና አለው፡፡
የኪነ ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ለአብነትም ኪነ ጥበብ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲካተት መደረጉን አንስተዋል፡፡
ይህም ተማሪዎች ጥበብን ከታች ክፍል ጀምረው አውቀውና ተገንዝበው ዘርፉን ይበልጥ ወደውት እንዲያድጉ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ኪነ ጥበበ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም እየተሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በቅርቡ ከውጪ ባለሙያዎች መጥተው በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ፊልም እንዴት መስራት እንደሚቻል ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
በሁሉም ሥራዎች የኪነ ጥበብን አላማ በትክክል መጠቀም ይገባል፤ ለዚህም መንግስት በትብብር ለመስራት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
የብሔር እና የሃይማኖት ጉዳይ ሲነሳ ነገር የሚያባብሱ ባለሙያዎች እንዳሉ አንስተው÷ ኪነ ጥበብን ለአፍራሽ ዓላማ ሳይሆን ለትውልድ ግንባታ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡
በኪነ ጥበብ ብሶትን ሳይሆን ቁጭትን ለማሳየት መስራት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በጥበብ ኢትዮጵያ ለምን ከድህነት መላቀቅ አቃታት የሚል ቁጭትን ማሳየት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
የጥበብ ሰዎች ፖለቲካ ላይ ሳይሆን ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ማተኮር አለባቸው፤ ምክንያቱም የፖለቲካ ልዩነት ያላቸውን ቡድኖች በማህበራዊ ጉዳይ ተሳስረው ማግኘት ይቻላል ፤ ይህም መልዕክትን በሚገባ ለማስተላለፍ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ