ኪነ ጥበብ ለስልጣኔና ሀገር እድገት ጉልህ ሚና ይጫወታል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኪነ ጥበብ ለስልጣኔ እና ሀገር እድገት ጉልህ ሚና ይጫወታል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህንን ያሉት ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ከተወጣጡ የጥበቡ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ውይይት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይታቸው በዓለም ታሪክ ስልጣኔን ያመጡና ብልጽግናን ያረጋገጡ በእኛም ታሪክ እንደተገለጡ ከኪነ ጥበብ የወጣ ሥራ እንዳልሰሩ አስታውሰዋል፡፡
ኪነ ጥበብ ተፈጥሮን የማድነቅና ያየውን ነገር በተለየ መንገድ በጽሑፍ፣ በሙዚቃና በስዕል የመግለጽ አቅም ስላለው የትም ዓለም ስልጣኔ ከጥበብ ውጪ አለመምጣቱን አስገንዝበዋል።
ኪነ ጥበብ ማደግ ለሚፈልግ የትኛውም ሀገር ኢትዮጵያን ጨምሮ ወሳኝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም አርቲስቶች የኪነ ጥበብን ካባ አክብረው መያዝ ሲችሉ ከሆነ ነው ብለዋል።
ባደጉት ሀገራት ሦስቱ አካላት ተቀናጅተው ቁም ነገር ይሰራሉ፤ እነዚህም ኪነ ጥበብ፣ ኢንዱስትሪና መንግስት መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኪነ ጥብቡ ሐሳብ ያፈልቃል፣ አኗኗር፣ አመጋገብ፣ አለባበስን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች በተለያየ መንገድ ይገልጻል ብለዋል።
ኢንዱስትሪው ደግሞ ኪነ ጥበብን በመከተል ያመርታል፤ ይህም ኪነ ጥበብ ተመልሶ እንዲሸጥ ያደርገዋል፤ በዚህ ወቅትም ንግድ ስለሚሳለጥ መንግስት ገንዘብ ያገኛል፣ ዐውድ ያመቻቻል፣ ሕግ ያስከብራል ሲሉ አብራርተዋል።
እነዚህ ሦስቱ አካላት ተስማምተው በሰሩባቸው ሀገራት የተለያዩ ቁምነገሮች ተከናውነዋል፤ ሦስቱ ተነጣጥለው ብቻቸውን ከሆኑ ግን ሙሉ እንደማይሆን አንስተዋል።
በዘርፉ የሚጎሉ ነገሮችን ለማሟላት መንግስትና የኪነ ጥበቡ ማኅበረሰብ አንድ ላይ የኢትዮጵያን ብልጽግናና የልጆቻችንን እጣ ፈንታ ለመስራት አብረን እንስራ ብለዋል።
በአድማሱ አራጋው