የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ገዢ ትርክትን የመገንባት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ገዢ ትርክትን የማስረጽ እና አመለካከትን የመቅረጽ ሚናቸውን በተገቢ ሁኔታ ሊወጡ ይገባል አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመላው ኢትዮጵያ ከተወጣጡ የጥበቡ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ ኪነ ጥበብ ገዢ ብሔራዊ ትርክት እና አንድነትን ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ዘርፍ አመለካከት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበት ጠቁመው÷ ጥበብ የችግር ጊዜ መሸጋገሪያ ድልድይ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ጥበብ መጤ ባሕልን የሚከላከል ብቻ ሳይሆን የተደበቁ ምርጥ የማህበረሰብ ባህሎች እና እሴቶችን ለማንጸባረቅ ጉልህ ሚና እንዳለው አውስተዋል፡፡
መጤ ባህሎች በብዙ መንገድ እየወረሩን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ እነዚህን ችግሮችን ለመከላከልም የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪ ላይ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ጥበብ ማለት በሆነ አጀንዳ ላይ ሃሳብ ሰጥቶ አነጋጋሪ እና አወዛጋቢ በመሆን ታዋቂነትን ለማግኘት መጣር እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡
አርቲስት የሰዎችን ስሜት የሚያንጸባርቅ የራሱ የሆነ ውብ የቋንቋ አጠቃቀም እንዳለው ገልጸው÷ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ አክቲቪዝምና አርቲስትነትን የመቀላቀል ሁኔታ እንደሚስተዋል ጠቁመዋል፡፡
ለኪነ ጥብብ እድገት በትብብር መስራት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ዘርፉን ለሀገር እድገት፣ ለትውልድ ግንባታ እና ገዢ ትርክትን ለማስረጽ መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ዘርፉ አካታችነት ባለው መልኩ ትልቅ ማህበር መመስረት እንደሚጠበቅበት ጠቁመው÷ ይህም ጥያቄዎችን በተገቢ ሁኔታ ለመመለስ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በመላኩ ገድፍ