ክልሉ ባለፉት 11 ወራት ከ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፋር ክልል ገቢዎች ቢሮ ባለፉት 11 ወራት ከ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ችያለሁ አለ።
በክልሉ በበጀት አመቱ በገቢ አሰባሰብ የተሻለ አፈፃፀም ማሳየት መቻሉን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ እድሪስ ሳሊህ ለፋና ዲጅታል ገልጸዋል፡፡
በዚህም ባለፉት 11 ወራት ከ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ያሉ ሲሆን፥ የዕቅዱን 103 በመቶ አፈጻጸም መመዝገቡን ተናግረዋል።
ይህንን ለማሳካት በሚያግዙ ስራዎች ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን በመግለጽ በንግዱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ክትትል በማድረግና በቢሮው በኩል የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማሳለጥ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የቢሮው ኢንተለጀንስ ቡድን እና የኦፕሬሽን ባለሙያዎች እስከ ታች ድረስ በመውረድ ክትትል ሲደረግ እንደነበርና በደረሰኞች የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች እንዲቀንሱ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡
ማህበረሰቡ ግብይት በደረሰኝ እንዲያከናውንና ነጋዴውና ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግብር መክፈል ጥቅሙ ለራሳቸው እንደሆነ በመረዳት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
በዮናስ ጌትነት