የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 10ኛው የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ጉባኤ ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ጉባኤውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ የአፍሪካ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ጉባኤ በሕብረቱ አባል ሀገራት በየሁለት ዓመቱ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያም በዚምባቡዌ በተካሄደ 9ኛው ዙር ጉባኤ ባደረገችው ውድድር የ10ኛውን ዙር ለማዘጋጀት መመረጧን አስታውሰዋል፡፡
ለሦስት ቀናት የሚካሄደው ጉባኤ የተከማቹ የአገልግሎት አቅርቦት ችግሮች በመፍታት አካታችና ዘላቂ ልማት ለማምጣት፣ ተጠያቂነት ለማስፈን እና የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት እና አፍሪካ ሕብረት ያወጧቸውን የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደርን የተመለከቱ አጀንዳዎች ለማስፈፀም የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ማድረጓንም ጠቁመዋል፡፡
የመጀመሪያው ዙር የማሻሻያ ፖሊሲ ማዕቀፍ በስምንት ተቋማት መጀመሩንም አመላክተዋል፡፡
በመቅደስ ከበደ