የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመኑ ምርጥ ተጫዋች የመጨረሻ እጩዎች ይፋ ሆኑ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመኑ ምርጥ ተጫዋች የመጨረሻ ስድስት ዕጩዎች ዝርዝር ይፋ ሆኗል፡፡
በሊጉ 15ኛ ደረጃን በመጨረስ አስከፊ የውድድር አመትን ያሳለፈው የማንቼስተር ዩናይትድ አማካይ ብሩኖ ፈርናንዴስ ከእጩዎቹ ዝርዝር ውስጥ ተካቷል።
ብሩኖ ለቀያይ ሰይጣኖቹ ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አቀብሏል።
የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል ተጫዋቾች ሞሃመድ ሳላህ እና አሌክሲስ ማካሊስተር ከስድስቱ እጩዎች መካካል ናቸው፡፡
27 ግቦችን በ42 ጨዋታዎች ያስቆጠረው የኒውካስል ዩናይትድ የፊት መስመር ተጫዋቹ አሌክሳንደር ኢሳክ በእጩዎቹ ውስጥ ተካቷል፡፡
በተመሳሳይ የአርሰናሉ ዴክላን ራይስ እና የቼልሲው ኮል ፓልመር የመጨረሻ እጩዎቹ ውስጥ መካተታቸውን የዘገበው ቢቢሲ፤ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር የውድድር ዘመኑ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት በቀጣይ ነሃሴ ወር ይፋ እንደሚሆን ገልጿል።
በአቤል ንዋይ