ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አንጎላ ሉዋንዳ ገቡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የአፍሪካና የአሜሪካ የቢዝነስ ጉባዔ ላይ ለመታደም አንጎላ ርዕሰ መዲና ሉዋንዳ ገብተዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ ሉዋንዳ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የዘንድሮውን የአፍሪካና የአሜሪካ የቢዝነስ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ አፍሪካን በተመለከተ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ድጋፍን መሰረት ካደረገ ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለመቀየር መወሰኑን ተከትሎ የሚካሄድ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
በጉባዔው የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የቢዝነስ መሪዎችን ጨምሮ 1 ሺህ 500 ተሳታፊዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡
ጉባዔው በአፍሪካና በአሜሪካ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችና ዕድሎች ዙሪያ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው።
በጉባዔው ፕሬዚዳንት ታዬ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን÷ ጎን ለጎንም የተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደሚያደርጉ ኢዜአ ዘግቧል።