Fana: At a Speed of Life!

የጤናው ዘርፍ በሚጠበቀው ልክ እንዲለወጥ አብዝተን እንፈልጋለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ውስጥ የጤናው ዘርፍ እንዲለወጥ አብዝተን እንፈልጋለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተወጣጡ የጤና ባለሞያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፥ በሀገሪቱ የጤና መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት የተሰሩ ሥራዎችን አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በድምሩ ከ6 ሺህ በላይ አዳዲስ ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች መገንባታቸውንና የማስፋፊያና የእድሳት ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

ከ350 ጤና ኬላዎች፣ ከ100 በላይ ጤና ጣቢያዎች፣ 190 ሆስፒታሎች እና 11 ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች መገንባታቸውን ጠቅሰው ፥ 1 ሺህ 800 ገደማ የጤና ተቋማት ላይ የማስፋፊያና የእድሳት ሥራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በየአካባቢው ያሉ የበሽታ ሥርጭትና መሰል መረጃዎችን ከግምት በማስገባት 15 ያህል የጤና ላቦራቶሪዎች መገንባታቸውንና ውሃ እና የሶላር አገልግሎት የሌላቸው ከ1 ሺህ በላይ የጤና ተቋማት አገልግሎቱን እንዲያገኙ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

እነዚህን ሥራዎች ማሳደግ ቢቻል የእኔም ፍላጎት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ ነገር ግን ምንም አልተሰራም ማለት ትክክል እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤና ተቋማትን ለሰራተኞቻቸው ምቹ የስራ ከባቢ ማድረግ በሚል እሳቤ የግሉን ዘርፍ በማስተባበር በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እድሳት ማስጀመራቸውን አስታውሰው ፥ ይህንን ጥረት ማስፋፋት ከዘርፉ ተቋማት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕክምና እንዲለወጥ አብዝተን እንፈልጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ የፍላጎት ችግር ባይኖርም የአቅም ውስንነት እንዳለ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ከ22 ሺህ በላይ የመንግስት የጤና ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰው÷ እነዚህን ሁሉ ተቋማት በመንግስት አቅም ማደስ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

በጤናው ዘርፍ ሰው እየተቀጠረ አይደለም በሚል የሚቀርቡ ጥያቄዎች ቢኖሩም የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ባለፉት ስድስት ዓመታት በእጥፍ ማደጉን ነው ያነሱት፡፡

ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ 219 ሺህ የጤና ባለሙያዎች እንደነበሩ አስታውሰው፥ በአሁኑ ወቅት በእጥፍ አድጎ ከ520 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በእነዚህ የለውጥ ዓመታት በጤና ዘርፍ በሰው ኃይል፣ በፋይናንስ፣ በመሰረተ ልማት እና የግሉን ዘርፍ ለማገዝ ለተደረገው ጥረት እውቅና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.