ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን መቋቋምና ምላሽ መስጠት የሚችሉ ተቋማትን መፍጠር ይገባል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ላይ የሚስተዋሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን መቋቋምና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚችሉ ጠንካራ ተቋማትን መፍጠር ይገባል አሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡
ኢትዮጵያ ከሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በትይዩ ያስተናገደቻቸው 10ኛው የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ቀጣናዊ ፎረም ዛሬ ተጠናቅቀዋል።
አቶ አደም ፋራህ በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ÷ በትይዩ የተካሄዱት ሁለቱም መርሐ ግብሮች በስኬት መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
በዓለም ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን መቋቋምና ቀድሞ ምላሽ መስጠት የሚችሉ ጠንካራ ተቋማትን መፍጠር ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለውን ውስብስብነት ከግምት ያስገቡ አዳዲስ ፈጠራዎችና ሞዴሎችን ገቢራዊ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የመንግሥት አገልግሎት በአፍሪካ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው÷ በአገልግሎት ሰጪዎች ላይ የክህሎት፣ የአመራር እና የትብብር አቅምን ማጎልበት ለሀገራዊ ሽግግር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
የኮንፍረንሱ ዓላማ የተቋም ግንባታ ብቻ ሳይሆን ለዜጎች ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ሃላፊነት ጭምር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጽንሰ ሃሳብ ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት የመነጨ መሆኑን ያነሱት አቶ አደም ÷ እስካሁን ባለው ሒደት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።