ሲዳማ ክልል ከ38 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ አቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሲዳማ ክልል በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 38 ሺህ 487 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ አቅርቧል፡፡
የክልሉ የቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግና ጥራትን ለማሻሻል የተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት አስገኝተዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት 40 ሺህ 128 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው ፥ በ11 ወራት ውስጥ 38 ሺህ 487 ቶን ቡና መቅረቡን ተናግረዋል፡፡
ይህም በበጀት ዓመቱ ከተያዘው እቅድ አንጻር አፈጻጸሙ 96 በመቶ መሆኑንና በቀሪ ጊዜያት እቅዱን ለማሳካት እንደሚሰራ ነው ያስረዱት፡፡
በክልሉ የቡና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር ጥራት ያላቸው ችግኞችን ከማዘጋጀት ጀምሮ የምርት ጥራትን የሚያሳድጉ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቦ ግብረ መልስ ከተሰጠበት 32 ሺህ 363 ቶን የቡና ምርት ውስጥ ከ99 በመቶ በላይ የሚሆነው ከ1ኛ እስከ 3ኛ የጥራት ደረጃ ማግኘቱንም አመልክተዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ