Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግንቦት እና ሰኔ ወር ያከናወኑት ተከታታይ ተግባራት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በግንቦት እና ሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ቁልፍ የሆኑ የኢኮኖሚ ልማት፣ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ዕድገት፣ ስትራቴጂካዊ ዲፕሎማሲ እና መንግሥታቸው ለዘላቂ ሀገራዊ ልማት እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በሚያሳይ መልኩ ተከታታይ ተግባራትን አከናውነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ወር እንደ ሀገር የውይይት እና የሠለጠነ የፖለቲካ ባህል እየጎለበተ እንዲመጣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይቶችን አካሂደዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የናይጄሪያውን ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማን ጨምሮ፤ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በተገኙበት የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በይፋ አስጀምረዋል።

የወሩ ተግባር የተጀመረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት የኢትዮጵያን ታላቁን የክብር ኒሻን ለቢል ጌትስ በመሸለም ነው። ይኽ የከበረ ሽልማት የጌትስ ፋውንዴሽን ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ላበረከታቸው አሻጋሪ ሥራዎች እና ታላላቅ ዘመን ተሻጋሪ በጎ ተጽዕኖዎችን ያከበረ ነዉ። ፋውንዴሽኑ በጤና፣ ግብርና፣ በዲጂታል መታወቂያ የሚያደርገው ጥረት ብሎም ጠንካራው በመከባበር ላይ የተመሠረተውን ትብብር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንሥተዋል።

የልማት እንቅስቃሴን በተመለከተ የገጠሩን ማኅበረሰብ አኗኗር ለማሻሻል የተጀመረው የገጠር ኮሪደር በሁሉም አካባቢዎች እየተስፋፋ መጥቷል። በዚህም በሰኔ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ የዞን ቀበሌዎች የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆኑ ሞዴል የገጠር መንደሮች ግንባታን አስጀምረዋል። ሞዴል የገጠር መንደሮቹ ቀላል ወጪ የሚጠይቁና በአካባቢው በሚገኙ ግብአቶች የሚገነቡ ሲሆኑ አርሶ አደሩም ጤናማና ክብር ያለው ሕይወት እንዲኖር የሚያስችሉ ናቸው።

በእነዚህ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ልማት ሥራዎችንም ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም ከዚህ ቀደም በጎርፍና ድርቅ አደጋ ይታወቁ የነበሩ አካባቢዎች ወደ ልማት ተምሳሌትነት ያደረጉትን ሽግግር ተመልክተዋል። በአካባቢዎቹ በተለይ በበቆሎ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች እጅግ አበረታች ናቸው።

በዚሁ ሰኔ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካከናወኗቸው ትልልቅ ተግባራት መካከል አንዱ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉት ልዩ አራት ክፍሎች ያሉት ሰፊ ቃለ መጠይቅ ሲሆን፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ እንደ ሀገር የተመዘገቡ ስኬቶችን እና የገጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም ችግሮችን ለመሻገር የተወሰዱ ርምጃዎችን በተመለከተ አብራርተዋል። በዚህ ቃለ መጠይቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ቀጣይ የዕድገት እና የብልጽግና ጉዞና መዳረሻን አመላክተዋል።

ሌላኛው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወሳኝ የሰኔ ወር ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ነው። በዚህ የዲፕሎማሲያዊ ክንውን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከናይጀሪያው ባለ ሀብት ጋር በነበራቸው ቆይታ ለኢትዮጵያ ወሳኝ የሆኑ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚያስችሉ ስልታዊ የኢንቨስትመን መስኮች ላይ ውይይት አድርገዋል። እንዲሁም የአሜሪካ ማሪን ኮርፕስ ጄኔራል እና አፍሪኮም አዛዥ ከሆኑት ጄነራል ማይክል ላንግሌይ ጋር የጋራ ፍላጎት በሆኑ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ሲቀጥል፤ በዚሁ ሰኔ ወር ውስጥ ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ (IAEA) ዋና ዳይሬክተር ማሪያኖ ግሮሲ ጋር ተገናኝተዋል። የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል በኢትዮጵያ የሚያደርገው ድጋፍ በካንሰር ሕክምና እክብካቤ፣ የእንስሳት ጤና፣ የፀፀ ፍላይ ማጥፊያ፣ በኒኩለር ኢንጂነሪንግ እና የቁጥጥር ማሕቀፎች ላይ ያተኮረ ነው። በዚህም የሁለቱ ውይይት በመካሄድ ላይ ባሉ ድጋፎች እና የወደፊት የትብብር ዕድሎች ላይ ያተኮረ ነበር።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሰኔ ወር እንደ ሀገር የውይይት እና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እየጎለበተ እንዲመጣ ከተለያዩ ቁልፍ ባለደረሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይቶችን አካሂደዋል። በዚህም መሠረት ከተፎካከሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጥበቡ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ ከመምህራን ተወካዮች፣ ከሚዲያ ባለሞያዎች፣ ከጤናው ዘርፍ ተወካዮች እና ሌሎች የኅብረተሰብ አካላት ጋር መክረዋል። በምክክር ሂደቱም በየዘርፉ ያሉ እድሎች እና በጎ ርምጃዎች ብሎም ክፍተቶች እና ተግዳሮቶች የተዳሰሱበት ነበር።

ሌላኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሰኔ ወር ልዩ ትኩረት ሰጥተው የተንቀሳቀሱበት እና የተለያዩ አቅጣጫዎች ያስቀመጠበት መስክ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ዕድገት ነበር። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የሳይንስ ሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ክፍል በይፋ ተከፍቷል። ይኽ ድንቅ ክንውን በአርቴፈኢሻል ኢንተሊጀንስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኢትዮጵያ ምላሽ፣ ግብርና፣ የውኃ ኃይል እና ኢነርጂ፣ ኤሮኖቲክስ እና አቪየሽን ላይ ያተኮሩ አምስት የዐውደ ርዕይ ምድቦችን የያዘ ነው። ይኽም ሀገራችን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ያላትን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።

በተጨማሪም በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የህዋ ቅርጽ ሉላዊ የትዕይንት አዳራሽም ይፋ ሆኗል። በ1000 ሜትር ስኩዌር ሜትር እና 36 ሜትር ዲያሜትር ይዞ ያረፈው አዳራሽ ዘመኑን በዋጀ የ4k ዲጂታል ምስል ማሳያ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ነው። ምስለ ሕዋው ከፍተኛ ጥራት ያለው እጅግ አስደማሚ ምስሎችን በማቅረብ የህዋውን አለም እጅግ አቅርቦ ያሳያል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ልማት ቁልፍ ብሄራዊ ፕሮጀክቶች የሆነውን፤ የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “በመትከል ማንሠራራት” በሚል መሪ ቃል በይፋ አስጀምረዋል። የአረንጓዴ ዐሻራ እጅግ ዘርፈ ብዙ ትርፋቶችን ያስገኘ ሥራ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ከሚተከለው ችግኝ ጋር ከ47.5 ቢሊዮን ገደማ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ይሄም በሚቀጥለው ዓመት ከምንተክለው ጋር ሲደመር 54 ቢሊየን መድረስ ያስችላል።

በጥቅሉ በዚህ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዋና ዋና ዘርፎች ሰፋ ያሉ ክንውኖች ያካሄዱበት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ አካባቢ ጥበቃ አንዲሁም በዲጂታል እና ፈጠራ መስክ ተግባረዊ ርምጃ እንዲኖር ውሳኔ ያሳለፉበት ወር ነበር። ሁሉም ተግባራት ለኢትዮጵያ ዕድገት እውን ለማድረግ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለትን አስፈላጊነት ለማጉላት የታለሙ ስኬታማ ክንውኖች ነበሩ።

#PMOEthiopia

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.