ስፖርት ለብሔራዊ አንድነት ሚናውን እንዲወጣ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የስፖርቱ ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታና ለብሔራዊ አንድነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ በትብብር እየተሰራ ነው አሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚያዘጋጀው ስለኢትዮጵያ መድረክ “ስፖርት ለአሸናፊ ሃገር” በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ዳር ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የስፖርት ባለሙያዎች፣ አሰልጣኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የስፖርቱ ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታና ለብሔራዊ አንድነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ስፖርት ብቁና ንቁ ዜጋ መፍጠር ያስችላል ያሉት ሚኒስተሯ ÷ ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው ፥ መንግስት የስፖርት ዘርፉን ሁለንተናዊ ፋይዳ በመረዳት ትኩረት ሰጥቶ እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ምቹ የስፖርት ሜዳዎችን ከመገንባት ጀምሮ ለስፖርት ዘርፉ ዕድገት አስቻይ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት መደረጉን ነው ያስረዱት፡፡
የስፖርቱ ዘርፉ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በከተሞች እድገት፣ በቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች ያለው አስተዋጽኦ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት እንደሚገባ በመድረኩ ተመላክቷል።
በደሳለኝ ቢራራ