ምቹና ማራኪ አካባቢን ለመፍጠር የሁሉም ድርሻ መሆን ያለበት የጽዳት ባህል …
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ (ኢ/ር) ጽዳትን ባህል በማድረግ ምቹ እና ማራኪ አካባቢ መፍጠር የሁሉም ድርሻ መሆን አለበት አሉ።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ በተገኙበት “ፅዳትን ባህል እናድርግ” በሚል መሪ ሀሳብ የፅዱ ኢትዮጵያ የንቅናቄ መርሃ ግብር በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ሌሊሴ ነሜ (ኢ/ር) እንዳሉት፤ ከከተሞች መስፋፋትና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የአካባቢ ብክለት እየሰፋ መጥቷል።
በተለይም ከፕላስቲክ ምርቶች አጠቃቀም ጉድለት የተነሳ እየደረሰ ያለው ብክለት ተፈጥሮን እየጎዳ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም በከተሞች ቆሻሻ እየተበራከተ በመሆኑ ይህንን ለመከላከል በጋራ ፅዱ አካባቢን በመፍጠር ለመኖሪያ ምቹ እና ማራኪ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ፅዱ አካባቢን መፍጠር ትብብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በተለይም የአካባቢ ጥበቃ ላይ የወጡ ህጎችን መፈፀምና ማስፈፀም ብሎም ማስንገንዘብ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተጀመረው ንቅናቄም 15 ሚሊየን ሰዎችን ገፅ ለገፅ ለመድረስ እና በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ደግሞ 50 ሚሊየን ሰዎች ጋር ተደራሽ ለመሆን ታቅዷል ነው ያሉት።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በበኩላቸው፤ የ”ፅዱ ኢትዮጵያ” ንቅናቄ የተጀመሩ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች እንዲጎለብቱና ውጤት እንዲኖራቸው ትልቅ ሚና ስላለው የክልሉ መንግስት ሁለንተናዊ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።