የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ለቀጣናው ሰላም
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ኢትዮጵያ የቀይ ባህር አጋር ከሆነች በአካባቢው ብሎም በቀጠናው ሰላምን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ይናገራሉ።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ተመራማሪ አዲስ አለማሁ ለፋና ዲጂታል እንደገለፁት÷ ቀይ ባህር ከፍተኛ የባህር ላይ ውንብድና፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ይካሄድበታል።
በዚህ መልኩ በባህሩ ላይ የሚደረጉ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ ብሎም በቀጣናው ሀገራት ላይ አሉታዊ ጫና እና የብሔራዊ ደህንነት ስጋት የማስከተል ዕድላቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
ለአብነትም አል ሻባብን ጨምሮ ሌሎች ወሰን ተሻጋሪ አሸባሪ ቡድኖች በቀይ ባህር ቀጣና መንቀሳቀሳቸው ቀጣናው ችግሩን ለመከላከል የተጠናከረ የሰላም ማስከበር ተግባር እንዲያከናውን ያስገድደዋል ነው ያሉት።
በመሆኑም የቀጣናው ሀገራት ህብረት በመፍጠር የተቀናጀ ዘመቻ በማካሄድ ስጋቱን ማስወገድ ይችላሉ።
እንደ ተመራማሪው፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ ምላሽ ካገኘ መሰል ቡድኖችን እንቅስቃሴ በመግታት ለቀጠናው እና አካባቢ ሰላም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራታል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪ አቶ ሴነሳ ደምሴ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱ በአካባቢው የሚደረገውን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በቅርበት እንዳትከታተል አድርጓታል ብለዋል፡፡
በተለይም በቀይ ባህር ላይ ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ባህር በሚያቋርጡ ፍልሰተኞች ላይ የከፋ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንደሚፈጽሙ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የባህር ላይ ውንብድና እንደሚፈጸም ጠቅሰው፤ ይህንን ችግር ለመከላከል የተቀናጀ የሰላምና ደህንነት ተግባር መከናወን አለበት ነው ያሉት።
ለዚህም በቀጣናው የሰላም እና ደህንነት ተግባር የተሻለ ተሞክሮ ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ ምላሽ አግኝቶ አስተዋጽኦ ማበርከት የምትችልበት ዕድል መፈጠር እንዳለበት አመላክተዋል።
በርካታ ሀገራት አህጉር አቋርጠው በመምጣት በቀይ ባህር እንቅስቃሴ ቢያደርጉም፤ ከባህሩ ከ60 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንቅስቃሴ መገለሏ ፍትሃዊ አይደለም ብለዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት የባህር በርን በተመለከተ ቁርጠኛ ውሳኔዎችን ሊያሳልፍ እንደሚገባ እንዲሁም ጎረቤት ሀገራት በቀጣናዊ ትስስር እና የጋራ እድገት እሳቤ ለባህር በር ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ሊሰጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በሚኪያስ አየለ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!