Fana: At a Speed of Life!

ከንግስና እስከ ባላንጣነት – የቀድሞው የፓሪስ ንጉስ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፓርክ ዴ ፕረንስ “ምባፔ ንጉሳችን፥ ኩራታችን ነህ” ተብሎ ቢዘመርለትም ወደ ማድሪድ መኮብለልን ሲመርጥ “ከእኛ ይልቅ ገንዘብን መርጠሃል” ተብሎ በራሳቸው በፒኤስጂ ደጋፊዎች ተብጠልጥሏል፡፡

በስተመጨረሻ ከክለቡ ፒኤሰጂ ጋር የመለያየቱ ነገር ቁርጥ ሲሆን በደጋፊዎች በክብር መሸኘቱ ይታወሳል፡፡

የተወደሰበትን የቀድሞ ክለቡን በተቃራኒ ሊገጥም በሎስ ብላንኮዎቹ ማልያ ወደ ሜዳ የሚገባው ኪሊያን ምባፔ ከፓሪሱ ክለብ ጋር ያላሳካው የሀገር ውስጥ ዋንጫ የለም፡፡

ነገር ግን የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግን በፓሪስ ማሳካት ባለመቻሉ ባለ ትልቁን ጆሮ ዋንጫ በማለም ነበር የሻምፒየንስ ሊግ ንጉስ ወደ ሆነው ማድሪድ የኮበለለው፡፡

አዲስ የእግር ኳስ ህይወትና አዲስ ፈተና እፈልጋለሁ በማለት ከፓሪሱ ክለብ መለያየት እንደሚፈልግ ሲገልጽ፥ በክለቡ ደጋፊዎችና አመራሮች ብዙ ትችትን አስተናግዷል፡፡

ሆኖም ነገሮች የተገላቢጦሽ ሆነው ምባፔ ሪያል ማድሪድን በተቀላቀለበት ዓመት ፒኤስጂዎች ታሪካዊውን የሻምፒየንስ ሊግ ድላቸውን ማጣጣም ቻሉ፡፡

በግማሽ ፍጻሜው አርሰናልን በደርሶ መልስ አሸንፈው የሙኒኩን ትኬት ሲቆርጡ፥ ደጋፊዎች “ያለ ኪሊያን ምባፔ የተሻልን ነን” በማለት በስታዲየም ሲዘምሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ተጫዋቹ በቀድሞ ክለቡ የሻምፒየንስ ሊግ ድል ማግስት ከክለቡ በመልቀቁ ይጸጽተው እንደሆን ተጠይቆ “የምጸጸትበት ምክንያት የለም ለክለቡ ማድረግ የምችለውን አድርጌያለሁ፥ አሁን ስላለሁበት የእግር ኳስ ምዕራፍ ነው የማስበው” በማለት ነበር በቀድሞ ክለቡ ድል መደሰቱን የገለጸው፡፡

ኪሊያን ምባፔ በፈረንጆቹ 2020 ፒኤስጂ በባየርን ሙኒክ ተሸንፎ ዋንጫውን ካጣበት የማድሪዱ የሻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ በኋላ በሰጠው አስተያየት፥ “ከዚህ ክለብ ጋር ይህንን ክብር ማሳካት እፈልጋለሁ ቢልም አብዝቶ የተመኘው ሳይሰምር ወደ ስፔን አቅንቷል፡፡

በዓለም የክለቦች ዋንጫ ለፍጻሜ ለማለፍ በሚደረገው የሪያል ማድሪድ እና የፒኤስጂ ትንቅንቅ ምባፔ የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ ለማስቆጠር ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

በአስደናቂ ብቃት ላይ የሚገኘው የሊዊስ ኤንሪኬ ቡድን በውድድሩ እስካሁን ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች የተቆጠረበት ግብ አንድ ብቻ ሲሆን ይህም በውድድሩ አነስተኛ ግብ የተቆጠረበት ክለብ ያደርገዋል፡፡

በአራት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያልተቆጠረበት የሻምፒየንስ ሊጉ ባለክብር ዛሬ ምሽትስ በኪሊያን ምባፔ በሚመራው የሎስ ብላንኮዎቹ የፊት መስመር ግብ ሳያስተናግድ መውጣት ይችላል ወይ የሚለው ይጠበቃል፡፡

ኪሊያን ምባፔ በ2017 ከሞናኮ ወደ ፒኤስጂ ከተዘዋወረ በኋላ ለፓሪሱ ክለብ በሁሉም ውድድሮች 308 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ በመጫወት 256 ጊዜ ኳስና መረብን አገናኝቷል።

ምባፔ ያልተከፈለኝ 55 ሚሊየን ዩሮ አለ በማለት በቀድሞ ክለቡ ፒኤስጂ ላይ ባለፈው ግንቦት ወር ክስ መስርቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ አሁን ላይ ጉዳዩን በንግግር ለመፍታት ክሱን ማቋረጡ ነው የተነገረው።

ዛሬ ምሽት 4፡00 ላይ ኪሊያን ምባፔ ከቀድሞ ክለቡ ጋር የሚገናኘውና በፍጻሜው ቼልሲን የሚገጥመውን ክለብ የሚለየው የሪያል ማድሪድ እና ፒኤስጂ ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.