በ2025 የዓለም የሰርከስ ውድድር ላይ ለሚሳተፈው ልዑክ ሽኝት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በ2025 የዓለም የሰርከስ ጥበብ ውድድር ላይ ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ሽኝት አድርገዋል፡፡
ኢትዮ ዊንጌት ራሽያን ስዊንግ የተሰኘው የሰርከስ ቡድን ኢትዮጵያን በመወከል በሞስኮ በሚካሄደው የዓለም የሰርከስ አርት ውድድር ላይ ይሳተፋል፡፡
በዚህ ዓመት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ15 ሀገራት የተውጣጡ 200 የሰርከስ ጥበብ አርቲስቶች የሚሳተፉ ሲሆን፥ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ኢትዮጵያን ለሚወክሉ የሰርከስ ቡድን አባላት ሽኝት አድርገዋል፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የሰርከስ ጥበብ ለጤናና ለአዕምሮ ንቃት ካለው ጥቅም ባሻገር ሀገራዊ ገጽታን በመገንባትና ሀገርን በማስተዋወቅ ረገድ አይተኬ ሚና ይጫወታል፡፡
በኢትዮጵያ የሰርከስ ሙያ እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከዘርፉ በሰፊው ተጠቃሚ ለመሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ የሀገራችንን ስም በማስጠራት በድል እንዲመለስ መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡