በሐረሪ ክልል ከ3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐረሪ ክልል በ2017 በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ እንዳሉት÷ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚታቀዱ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ አለበት።
በመሆኑም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የክልሉን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ ዘርፍ ብዙ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም 3 ቢሊየን 116 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 3 ቢሊየን 108 ሚሊየን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 99 ነጥብ 75 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልፀዋል።
በቀጥታ ታክስ ከ1 ቢሊየን 726 ሚሊየን ብር በላይ፣ ቀጥታ ካልሆነ ታክስ 797 ሚሊየን ብር፣ ታክስ ነክ ካልሆነ ገቢ 128 ሚሊየን ብር እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከ456 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
የተሰበሰበው ገቢ ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ38 ነጥን 5 በመቶ ብልጫ አለው ነው ያሉት።
ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን መዘርጋት፣ ውዝፍ እዳን አሟጦ መሰብሰቡ እና የቅሬታ አፈታት ስርዓትን ማሻሻል መቻሉ ለገቢው ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
የአሰራር ሥርዓት ላይ የነበሩ መመሪያዎችን በማሻሻል እና ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር የማስገባት ሥራ በትኩረት መከናወኑ የገቢ መሰብሰብ አቅምን ጨምሯል ብለዋል።
በ2018 የበጀት ዓመት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ዝግጅት መደረጉን መናገራቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሔኖክ ሙሉነህ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።