በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለ5 ሚሊየን ሰዎች ነፃ የጤና ምርመራ ይሰጣል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጤና ዘርፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 5 ሚሊየን ሰዎች ነፃ የጤና ምርመራ ለመስጠት ታቅዷል፡፡
የ2017 የጤናው ዘርፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተጀምሯል፡፡
በዘርፉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ነፃ ምርመራ፣ ችግኝ ተከላ እና የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ይከናወናል።
በተጨማሪም ለ6 ሺህ ዜጎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ ደም ልገሳ፣ ማዕድ ማጋራት፣ የህሙማን ምገባ፣ ዳያስፖራውን በማስተባበር የቀዶ ጥገና ህክምና፣ የህክምና መሳሪያዎች ጥገና እና መሰል ተግባራት እንደሚከናወኑ ተጠቁሟል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በወቅቱ እንዳሉት÷ የሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዘርፉን የዕለት ተለት ተግባራት ያጠናክራል።
አጋጣሚው ሀገራችንን እና ህብረተሰቡን በጥልቀት በማገልገል አሻራችንን የምናስቀምጥበት ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሙያዎች እና በጎ ፈቃደኞችን በማሰባሰብ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት መስጠት መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
በሴክተሩ የተከናወነው ዘርፈ ብዙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ገንዘብ ሊወጣባቸው የሚችሉ አገልግሎቶችን ለመሸፈን አስችሏል ነው ያሉት።
በዛሬው መርሐ ግብር ቀደም ሲል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተሳተፉ ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷል።
በቅድስት አባተ