Fana: At a Speed of Life!

404 ሺህ በላይ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች በአፋር ክልል…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋት የዘርፉን እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ፡፡

የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ አብዱ መሃመድ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪስት መስህብ ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስተዋወቅ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

የክልሉ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑትን ዳሎል፣ ኤርታሌ፣ አፍዴራ ሐይቅ፣ አላሎ ባድ ፈል፣ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ የአብዬ ሐይቅና ሌሎችን በማልማት ረገድ አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በቱሪስት መዳረሻዎች አቅራቢያ ለጎብኚዎች ማረፊያ የሚሆኑ ባሕላዊ የመዝናኛ ቤቶችንና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን የመገንባት ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዘርፉ በተለያዩ አካባቢዎች ባለሃብቶች በሆቴሎች እና ሎጂዎች ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ትኩረት መደረጉን ነው ያስረዱት፡፡

በክልሉ የሚገኘውን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ለማስተዋወቅና ከዘርፉ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትብብር መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡

ከለውጡ ወዲህ በክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይበልጥ በማልማት የውጭ እና የሀገር ውስጥ ቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት 4 ሺህ 300 የውጪ ቱሪስቶች በክልሉ የሚገኙ መስህቦችን እንደጎበኙ ጠቅሰው÷ በዚህም 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ከመግቢያ ክፍያ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል 400 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ዜጎች ክልሉን የጎበኙ ሲሆን÷ በዚህም በቱሪዝም ኮንፈረንስና ሌሎች አገልግሎቶች የክልሉን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማነቃቃት መቻሉን አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ያለው ሰላም የቱሪስት ፍሰቱ ከባለፉት ዓመትታ በተሻለ ሁኔታ እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አቶ አብዱ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.