ልዩነትን በውይይት የመፍታት ባህል ሊዳብር ይገባል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ልዩነትን ከግጭት በራቀ መልኩ በውይይት የመፍታት ባህል ሊዳብር ይገባል አሉ የሀይማኖት አባቶች።
በኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት አስተባባሪነት የሀይማኖት አባቶች በትግራይ መቐለ ያደረጉትን የሰላም ጥሪ በማስመልከት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ እንዳሉት፤ የሀይማኖት አባቶቹ በቆይታቸው ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጀነራል ታደሰ ወረደ እና አመራራቸው ጋር ተወያይተዋል።
እንዲሁም ከክልሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል።
የሀይማኖት አባቶቹ ለባለድርሻ አካላቱ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል።
የሀይማኖት አባቶቹ፣ በትግራይ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገራቸውን ጠቅሰው፤ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፍታት እንደሚገባ ማስገንዘባቸውንም አስረድተዋል።
ባለድርሻ አካላቱ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሚፈቱም ተስፋቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤም በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን በጎ አበርክቶ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያመለከቱት ሀጂ ኢብራሂም፤ ልዩነትን ከግጭት በራቀ አኳሃን በውይይት ብቻ የመፍታት ባህል በሁሉም አካባቢዎች ሊዳብር ይገባል ብለዋል።