የእንስሳትን ጤና በማሻሻል የዘርፉን ጠቀሜታ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንስሳትን ጤና በማሻሻል የዘርፉን ጠቃሜታ ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡
በሚኒስቴሩ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ የዳልጋና ጋማ ከብቶች ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል በትብብር እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም ከዘርፉ የሚገኘውን ጠቀሜታ ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመው ÷ በቀጣይ የእንስሳትን ጤና ይበልጥ ለማሻሻል ክትባት የመስጠትና ሌሎች ሥራዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የጋማ እንስሳት የሆኑ ፈረስ፣ በቅሎና አህያ ላይ የሚስተዋለውን የጤና ችግር ለመፍታት ከከተማ አስተዳደሩ እና ከኢልኔት ፋውንዴሽን ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በከተማዋ ፈረስ፣ በቅሎና አህያ በበሽታ ሲጎዱ ወይም አገልግሎት መስጠት ሲያቆሙ ወደ መንገድ እንደሚጣሉ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ሳቢም እንስሳቱ የከተማዋን ውበትና ጽዳት ከማጉደፍ ባሻገር ማሕበረሰቡን ለበሽታ እና ለትራፊክ አደጋ እየዳረጉ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
ችግሩን በመረዳትም ኢልኔት ፋውንዴሽን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ፈረስ፣ በቅሎና አህያ አገልግሎት ሲያቆሙ ወደ መንገድ የሚጣሉበትን ሁኔታ የሚያስቀር ተንቀሳቃሽ ክሊኒክ በቅርቡ ይፋ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ክሊኒኩ እንስሳቱ በተለያዩ በሽታዎች ከመጠቃታቸው በፊት ሕክምና ለመስጠት እና የማይድኑ ከሆነም ከመንገድ ዳር ሆነው ለትራፊክ እክል እንዳይፈጥሩ እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም እንስሳቱ በመዲናዋ እየተከናወነ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት እና የከተማዋ ጽዳትና ውበት ላይ አሉታዊ ጫና እንዳያሳድሩ ሚናው ጉልህ ነው ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ