Fana: At a Speed of Life!

 በምክክር ሒደቱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክክር ሒደቱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፡፡

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ÷ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክር ሒደቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ቢሆንም ጥቂቶቹ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ሳይሳተፉ ቆይተዋል።

ኮሚሽኑ ሁሉንም ወገን ያሳተፈ ምክክር ለማካሄድ ሳይሳተፉ የቆዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እያወያየ መሆኑን ጠቁመው÷ ከእናት ፓርቲ፣ ኢህአፓ እና መኢአድ ጋር ከሰሞኑ ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ፓርቲዎቹ እንዲፈቱ ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች መፍትሄ የሚያገኙ ከሆነ በምክክሩ እንደሚሳተፉ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡፡

በአንጻሩ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ቅድመ ሁኔታዎች ቀድመው መፈታት አለባቸው በሚል እየተሳተፉ አለመሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

ስለሆነም ኮሚሽኑ እነዚህን ፓርቲዎች በምክክር ሒደቱ ለማሳተፍ ተጨማሪ ውይይቶችን እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡

በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ወገኖች በምክክሩ እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ቃል አቀባዩ ÷ በዚህም ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ጋር ውይይት መደረጉንና በጉዳዩ ላይ ኮሚሽኑ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር እንደሚመክርበት ጠቁሟል ብለዋል።

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.