ኢኮኖሚያዊ ሪፎርሙን ዘላቂ እና አካታች ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊያድግ ይገባል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢኮኖሚያዊ ሪፎርሙን ዘላቂ እና አካታች ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊያድግ ይገባል አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ ትብብር ለማጠናከር፣ የፖሊሲ አቅጣጫ ላይ ግንዛቤን ለማሳደግና የኢንቨስትመንት እድሎችን ለመፈተሽ በማለም እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
በኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ወዲህ አንድ ዓመት የተጠጋው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ውጤታማነት ለማስቀጠል የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የፋይናንስ ዘርፉ አካታችነት፣ የብድር አቅርቦትን ማሻሻልና የኢንቨስትመንት ሪፎርም በዚህ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፥ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲኖር መንግስት በተናጠል የሚያደርገው እንቅስቀሴ በቂ አለመሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም በፋይናንስ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና ሌሎችም ዘርፎች የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ለዘላቂ እና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።
ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት ሀላፊዎችና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ተሳትፎን ያደረጉበት የፋይናንስ ጉባዔው ከፖሊሲ፣ ከአፈፃፀምና ከግንዛቤ በርካታ አኳያ ሀሳቦች የተነሱበት ነው።
ማክሮ ኢኮኖሚና መዋቅራዊ ማሻሻያ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርምና የኢንቨስትመንት ዕድሎችና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ የጉባዔው ቁልፍ አጀንዳዎች ናቸው።
በሚኪያስ አለሙ