Fana: At a Speed of Life!

እነ ቀሲስ በላይ በሙስና ወንጀል “ሊፈረድብን አይገባም” በማለት ባቀረቡት ይግባኝ ላይ ውሳኔ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት እነ ቀሲስ በላይ መኮንን በሙስና ወንጀል “ሊፈረድብን አይገባም” በማለት ባቀረቡት ይግባኝ ጥያቄ እና የዐቃቤ ሕግ የመልስ መልስ ላይ ውሳኔ ሰጠ።

ከአንድ ዓመት በፊት የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ቀሲስ በላይ መኮንን፣ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው እያሱ እንዳለ፣ በኮሚሽን ስራ ላይ የተሰማራው በረከት ሙላቱ እና አለምገና ሳሙኤል እንዲሁም የኒሞና ንግድ ስራ ኃላ/የተ/የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አበራ መርጋ በተባሉ ተከሳሾች ላይ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦ ነበር።

በዚህም እነ ቀሲስ በላይ መኮንን ከአፍሪካ ህብረት ምንም አይነት የክፍያ ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ ላይ ተከሳሾች በተለያየ መጠን ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የሚል የ6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ሀሰተኛ የክፍያ ሰነድ በአንደኛ ተከሳሽ አማካኝነት ለባንኩ መቅረቡ ተጠቅሶ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።

በዚህ መልኩ የቀረበውን ዝርዝር ክስ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ብቻ ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በአድራሻቸው ባለመገኘታቸውና በተደጋጋሚ ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ከዚህም በኋላ በነበሩ የተለያዩ የችሎት ቀጠሮዎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች እንዲሁም የተከሳሾቹን መከላከያ ማስረጃ ፍርድ ቤቱ መርምሮና አመዛዝኖ 1ኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ መኮንን በሙሉ ድምጽ፤ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ደግሞ በአንድ ዳኛ የሀሳብ ልዩነት በአብላጫ ድምጽ የጥፋተኛ ፍርድ ተሰጥቶ ነበር።

ከዚህም በኋላ የስር ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ወንጀሉ የተፈጸመው በትብብር መሆኑን ጠቅሶ ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ እንዲሁም ተከሳሾች ያቀረቡትን የተለያዩ ቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን በመየያዝ በጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በነበረ ቀጠሮ 1ኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ መኮንን በዕርከን 21 መሰረት በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ፤ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችን ደግሞ በዕርከን 17 መሰረት እያንዳንዳቸውን በ3 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑ ይታወቃል።

ተከሳሾቹ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ይግባኝ ወንጀል ችሎት “በሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ልንባል አይገባም” እንዲሁም “የስር ፍርድ ቤት የሰጠው የቅጣት መጠን ተገቢ አደለም” የሚል ይዘት ያለው አቤቱታ አቅርበዋል።

ችሎቱ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታ እና የዐቃቤ ሕግን የመልስ መልስ መርምሮ እነ ቀሲስ በላይ የሙስና አዋጅ 881/2007 አንቀጽ 32 (2) (3) መሠረት በከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ልንባል አይገባም የሚለው አቤቱታቸው ውድቅ ተደርጎ የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው የጥፋተኝነት ፍርድ ሥነሥርዓታዊ መሆኑን ጠቅሶ ፍርዱን አፅንቶታል።

በሌላ በኩል ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ በተከሳሾቹ ላይ ላይ በስር ፍርድ ቤት ተሰጥቶ የነበረው ቅጣት መጠንን በማማሻል ቀሲስ በላይ ከ5 ዓመት ወደ 3 ዓመት ከ7 ወር አስራት ተቀይሮላቸዋል።

ኢያሱ እንዳለ እና በረከት ሙላት የተባሉ ተከሳሾች ደግሞ በስር ፍ/ቤት የተወሰነባቸው 3 ዓመት ከ3 ወር የነበረው ቅጣት 3 ወር ብቻ ተቀንሶ 3 ዓመት ብቻ እንዲሆን ውሳኔ ተሰጥቷል።

በተጨማሪም ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ተከሳሾቹ አቅርበውት የነበረውን የቅጣት ገደብ ጥያቄ አልተቀበለውም።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.